ኢዩኤል 1:1-20

ኢዩኤል 1:1-20 NASV

ወደ ባቱኤል ልጅ ወደ ኢዩኤል የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤ እናንተ ሽማግሌዎች፣ ይህን ስሙ፤ በምድሪቱም የምትኖሩ ሁላችሁ፣ አድምጡ፤ በእናንተ ዘመንም ሆነ በአባቶቻችሁ ዘመን፣ እንዲህ ዐይነት ነገር ሆኖ ያውቃልን? ይህን ለልጆቻችሁ ተናገሩ፤ ልጆቻችሁ ለልጆቻቸው ይንገሩ፤ ልጆቻቸውም ለሚቀጥለው ትውልድ ይንገሩ። ከአንበጣ መንጋ የተረፈውን፣ ትልልቁ አንበጣ በላው፤ ከትልልቁ አንበጣ የተረፈውን፣ ኵብኵባ በላው፤ ከኵብኵባ የተረፈውን፣ ሌሎች አንበጦች በሉት። እናንተ ሰካራሞች፤ ተነሡ፤ አልቅሱ፤ እናንተ የወይን ጠጅ ጠጪዎች ሁሉ፤ ዋይ በሉ፤ ስለ አዲሱ የወይን ጠጅ ዋይ ብላችሁ አልቅሱ፤ አፋችሁ ላይ እንዳለ ተነጥቃችኋልና። ኀያልና ቍጥር ስፍር የሌለው ሕዝብ፣ ምድሬን ወሯታልና፤ ጥርሱ እንደ አንበሳ ጥርስ፣ መንጋጋውም እንደ እንስት አንበሳ መንጋጋ ነው። የወይን ቦታዬን ባድማ አደረገው፤ የበለስ ዛፎቼንም ቈራረጠ፤ ቅርንጫፎቻቸው ነጭ ሆነው እስኪታዩ ድረስ፣ ቅርፊታቸውን ልጦ፣ ወዲያ ጣላቸው። የልጅነት ዕጮኛዋን እንዳጣች ድንግል፣ ማቅ ለብሳችሁ አልቅሱ። የእህል ቍርባንና የመጠጥ ቍርባን፣ ከእግዚአብሔር ቤት ተቋርጧል፤ በእግዚአብሔርም ፊት የሚያገለግሉ፣ ካህናት ያለቅሳሉ። ዕርሻዎች ባዷቸውን ቀርተዋል፤ ምድሩም ደርቋል፤ እህሉ ጠፍቷል፤ አዲሱ የወይን ጠጅ ዐልቋል፤ ዘይቱም ተሟጧል። እናንተ ገበሬዎች፣ ዕዘኑ፤ እናንተ የወይን ገበሬዎች፣ ዋይ በሉ፤ ስለ ገብሱና ስለ ስንዴው አልቅሱ፤ የዕርሻው መከር ጠፍቷልና። ወይኑ ደርቋል፤ የበለስ ዛፉም ጠውልጓል፤ ሮማኑ፣ ተምሩና እንኮዩ፣ የዕርሻው ዛፎች ሁሉ ደርቀዋል፤ ስለዚህ ደስታ፣ ከሰው ልጆች ርቋል። ካህናት ሆይ፤ ማቅ ለብሳችሁ አልቅሱ፤ እናንተ በመሠዊያው ፊት የምታገለግሉ፣ ዋይ በሉ፤ እናንተ በአምላኬ ፊት የምታገለግሉ፣ ኑ፤ ማቅ ለብሳችሁ ዕደሩ፤ የእህል ቍርባኑና የመጠጥ ቍርባኑ፣ ከአምላካችሁ ቤት ተቋርጧልና። ቅዱስ ጾምን ዐውጁ፤ የተቀደሰንም ጉባኤ ጥሩ፤ ሽማግሌዎችን ሰብስቡ፤ በምድሪቱ የሚኖሩትን ሁሉ፣ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ጥሩ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ። ወዮ ለዚያ ቀን! የእግዚአብሔር ቀን ቀርቧልና፤ ከሁሉን ቻይ አምላክ እንደ ጥፋት ይመጣል። የሚበላ ምግብ፣ ከዐይናችን ፊት፣ ደስታና ተድላ፣ ከአምላካችን ቤት አልተቋረጠብንምን? ዘሩ በዐፈር ውስጥ፣ በስብሶ ቀርቷል፤ ግምጃ ቤቶቹ ፈራርሰዋል፤ ጐተራዎቹም ተሰባብረዋል፤ እህሉ ደርቋልና። መንጎች እንደ ምን ጮኹ፣ ከብቶቹ ተደናግጠዋል፤ መሰማሪያ የላቸውምና፤ የበግ መንጎች እንኳ ተቸግረዋል። አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ እጣራለሁ፤ ያልተነካውን መሰማሪያ እሳት በልቶታልና፤ የዱሩን ዛፍ ሁሉ ነበልባል አቃጥሎታል። የዱር አራዊት እንኳ ወደ አንተ አለኸለኹ፤ ወራጁ ውሃ ደርቋል፤ ያልተነካውንም መሰማሪያ እሳት በልቶታል።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}