ኢዮብ 38:1-21

ኢዮብ 38:1-21 NASV

እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰለት፤ እንዲህም አለው፤ “ዕውቀት በጐደለው ቃል፣ ዕቅዴን የሚያጨልም ይህ ማን ነው? እስኪ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፤ እኔ ልጠይቅህ፣ አንተም መልስልኝ። “ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ የት ነበርህ? በርግጥ የምታስተውል ከሆንህ ንገረኝ። ካወቅህ፣ መጠኗን ለይቶ ማን ወሰነ? በላይዋስ መለኪያ ገመድ የዘረጋ ማን ነው? መሠረቶቿ ምን ላይ ተተከሉ? የማእዘን ድንጋይዋንስ ማን አቆመ? ይህም የሆነው የንጋት ከዋክብት በዘመሩበት ጊዜ፣ መላእክትም እልል ባሉበት ጊዜ ነበር። “ባሕር ከማሕፀን በወጣ ጊዜ፣ በር የዘጋበት ማን ነው? ደመናውን ልብሱ፣ ጨለማንም መጠቅለያው አደረግሁለት፣ ድንበር ወሰንሁለት፤ መዝጊያና መወርወሪያውን አበጀሁለት። ‘እስከዚህ ድረስ ትመጣለህ፤ ማለፍ ግን አትችልም፤ የዕቡይ ማዕበልህም ገደብ ይህ ነው’ አልሁት። “ከተወለድህ ጀምሮ ንጋትን አዝዘህ ታውቃለህን? ወይስ ወጋገን ስፍራውን እንዲይዝ አድርገሃል? በዚህም የምድርን ዳርቻ ይዞ፣ ክፉዎችን ከላይዋ እንዲያራግፍ አድርገሃልን? ምድር ከማኅተም በታች እንዳለ የሸክላ ጭቃ ቅርጿ ይወጣል፤ ቅርጿ እንደ ልብስ ቅርጽ ጐልቶ ይታያል። ክፉዎች ብርሃናቸውን ተከልክለዋል፤ ከፍ ያለው ክንዳቸውም ተሰብሯል። “ወደ ባሕር ምንጭ ወርደህ ታውቃለህን? ወይስ ወደ ጥልቀቱ ገብተህ በመሠረቱ ላይ ተመላልሰሃልን? የሞት ደጆች ተገልጠውልሃልን? የሞትንስ ጥላ በሮች አይተሃልን? የምድርን ስፋት ታውቃለህን? ይህን ሁሉ ዐውቀህ ከሆነ፣ ንገረኝ። “ወደ ብርሃን መኖሪያ የሚያደርሰው መንገድ የትኛው ነው? የጨለማ መኖሪያስ ወዴት ነው? ወደ ማደሪያቸው ልትወስዳቸው ትችላለህን? የመኖሪያቸውን መንገድ ታውቃለህ? ያን ጊዜ ተወልደሃል! ዕድሜህ ትልቅ ነውና፣ አንተስ በርግጥ ሳታውቅ አትቀርም!