ኢዮብ 32:1-10

ኢዮብ 32:1-10 NASV

ኢዮብ በበኩሉ ራሱን እንደ ጻድቅ ቈጥሮ ስለ ነበር፣ እነዚህ ሦስት ሰዎች ለርሱ መልስ መስጠታቸውን ተዉ። ከራም ወገን የሆነው፣ የቡዛዊው የባርክኤል ልጅ ኤሊሁ ግን ኢዮብ ከእግዚአብሔር ይልቅ ራሱን ጻድቅ ስላደረገ እጅግ ተቈጣው። ሦስቱ የኢዮብ ጓደኞች በኢዮብ ላይ መፍረድ እንጂ፣ ነገሩን ሊያሳምኑት ስላልቻሉ፣ በእነርሱም ላይ ተቈጣ። ኤሊሁ፣ ሌሎቹ በዕድሜ ይበልጡት ስለ ነበር ከእነርሱ ቀድሞ ለኢዮብ ሳይናገር ቈየ። ነገር ግን ኤሊሁ እነዚህ ሦስቱ የሚሉትን ባጡ ጊዜ ቍጣው ነደደ። ስለዚህ የቡዛዊው የባርክኤል ልጅ ኤሊሁ እንዲህ አለ፤ “እኔ በዕድሜ ታናሽ ነኝ፤ እናንተ ግን አዛውንቶች ናችሁ፤ ከዚህም የተነሣ የማውቀውን ለመናገር አልደፈርሁም፤ ፈርቼ ዝም አልሁ። ‘ዕድሜ ይናገራል፤ ረዥም ዘመን ጥበብን ያስተምራል’ ብዬ ነበር። ነገር ግን በሰው ያለው መንፈስ፣ ሁሉን ቻይ አምላክ እስትንፋስ፣ ማስተዋልን ይሰጣል። ጠቢባን የሚሆኑት በዕድሜ የገፉ ብቻ አይደሉም፤ የሚያስተውሉም ሽማግሌዎች ብቻ አይደሉም። “ስለዚህ፣ ‘ስሙኝ፣ እኔም የማውቀውን ልንገራችሁ’ እላለሁ።