ኢዮብ 23
23
ኢዮብ
1ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፤
2“ዛሬም ሐዘኔ መራራ ነው፤
እያቃሰትሁ እንኳ እጁ#23፥2 በሰብዓ ሊቃናት ትርጕም፣ በሱርስትና በዕብራይስጡ ላይ፣ እጅ በላዬ ይላል። በላዬ ከብዳለች።
3እርሱን የት እንደማገኘው ባወቅሁ፤
ወደ መኖሪያውም መሄድ በቻልሁ!
4ጕዳዬን በፊቱ አቀርብ ነበር፤
አፌንም በሙግት እሞላው ነበር።
5የሚመልስልኝ ቃል ምን እንደ ሆነ ባወቅሁ ነበር፤
የሚለኝንም ባስተዋልሁ ነበር።
6በታላቅ ኀይሉ ከእኔ ጋራ ይሟገት ይሆን?
አይደለም፤ ይልቁን ያደምጠኛል።
7ቅን ሰው ጕዳዩን በርሱ ፊት ያቀርባል፤
እኔም ከፈራጄ ለዘላለም ነጻ እሆናለሁ።
8“ዳሩ ግን ወደ ምሥራቅ ብሄድ፣ በዚያ የለም፤
ወደ ምዕራብም ብሄድ፣ እርሱን አላገኘውም፤
9በሰሜን እየሠራ ሳለ አላየውም፤
ወደ ደቡብ በሚዞርበት ጊዜ ደብዛው አይገኝም።
10ግን እኔ የምሄድበትን መንገድ ያውቃል፤
ከፈተነኝም በኋላ እንደ ወርቅ እወጣለሁ።
11እግሮቼ ርምጃውን በጥብቅ ተከታትለዋል፤
ፈቀቅ ሳልል መንገዱን ጠብቄአለሁ።
12ከአፉ ከወጣው ትእዛዝ አልራቅሁም፣
የአንደበቱን ቃል ከዕለት እንጀራዬ አብልጬ ይዣለሁ።
13“እርሱ ግን ራሱን ችሎ ብቻውን የሚኖር ነው፤ የሚቋቋመውስ ማን ነው?
እርሱ የፈቀደውን ያደርጋል።
14በእኔ ላይ የወሰነውን ይፈጽማል፤
ይህን የመሰለ ዕቅድም ገና ብዙ አለው።
15በፊቱ የደነገጥሁትም ለዚህ ነው፤
ይህን ሁሉ ሳስብ እፈራለሁ።
16እግዚአብሔር ልቤን አባባው፤
ሁሉን ቻይ አምላክ አስደነገጠኝ።
17ይህም ሆኖ ሳለ ጨለማው፣
ፊቴንም የጋረደው ጽልመት ልሳኔን አልዘጋውም።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.