ይህን ካለ በኋላ፣ በምድር ላይ እንትፍ ብሎ በምራቁ ጭቃ አበጀ፤ የሰውየውንም ዐይን ቀባና፣ “ሄደህ በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ” አለው፤ ሰሊሆም ማለት “የተላከ” ማለት ነው። ሰውየውም ሄዶ ታጠበ፤ እያየም ተመልሶ መጣ። ጎረቤቶቹና ከዚህ ቀደም ብሎ ሲለምን ያዩት ሰዎች፣ “ይህ ሰው ተቀምጦ ሲለምን የነበረው አይደለምን?” አሉ። አንዳንዶቹም፣ “በርግጥ እርሱ ነው” አሉ። ሌሎችም፣ “ይመስለዋል እንጂ እርሱ አይደለም” አሉ። እርሱ ግን፣ “እኔው ነኝ” አለ። እነርሱም፣ “ታዲያ ዐይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም፣ “ኢየሱስ የሚሉት ሰው ጭቃ አድርጎ ዐይኔን ቀባኝ፤ ወደ ሰሊሆም ሄጄ እንድታጠብም ነገረኝ፤ ሄጄ ታጠብሁ፤ ማየትም ቻልሁ” ሲል መለሰ። እነርሱም፣ “ታዲያ፣ ያ ሰው የት አለ?” አሉት። እርሱም፣ “እኔ አላውቅም” አለ። እነርሱም ዐይነ ስውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። ኢየሱስ ጭቃ የሠራበት፣ የሰውየውንም ዐይን የከፈተበት ቀን ሰንበት ነበር። ስለዚህ ፈሪሳውያንም እንዴት ማየት እንደ ቻለ ጠየቁት። ሰውየውም፣ “እርሱ ዐይኔን ጭቃ ቀባኝ፤ እኔም ታጠብሁ፤ ይኸው አያለሁ” አላቸው። ከፈሪሳውያንም አንዳንዶቹ፣ “ይህ ሰው ሰንበትን ስለማያከብር፣ ከእግዚአብሔር አይደለም” አሉ። ሌሎች ግን፣ “ኀጢአተኛ፣ እንዲህ ያሉትን ታምራዊ ምልክቶች እንዴት ሊያደርግ ይችላል?” አሉ። በመካከላቸውም አለመስማማት ተፈጠረ። ስለዚህ፣ ዐይነ ስውር ወደ ነበረው ሰው ተመልሰው፣ “ዐይንህን ስለ ከፈተው ሰው፣ እንግዲህ አንተ ምን ትላለህ?” አሉት። ሰውየውም፣ “እርሱ ነቢይ ነው” አለ። አይሁድ ወደ ወላጆቹ ልከው እስኪያስጠሯቸው ድረስ፣ ሰውየው ዐይነ ስውር እንደ ነበረና እንዳየ አላመኑም ነበር። እነርሱም፣ “ዐይነ ስውር ሆኖ ተወልዷል የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታዲያ አሁን እንዴት ሊያይ ቻለ?” አሏቸው። ወላጆቹም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ልጃችን መሆኑንና ዐይነ ስውር ሆኖ መወለዱን እናውቃለን፤ አሁን ግን እንዴት ማየት እንደ ቻለና ዐይኖቹን ማን እንደ ከፈተለት እኛ አናውቅም። ሙሉ ሰው ስለ ሆነ፣ ስለ ራሱ መናገር ይችላልና እርሱን ጠይቁት።” ኢየሱስን፣ ክርስቶስ ነው ብሎ የመሰከረ ሁሉ ከምኵራብ እንዲባረር አይሁድ አስቀድመው ወስነው ስለ ነበር፣ ወላጆቹ ይህን ያሉት አይሁድን ፈርተው ነው። ስለዚህ ወላጆቹ፣ “ሙሉ ሰው ስለ ሆነ እርሱን ጠይቁት” አሉ። ዐይነ ስውር የነበረውንም ሰው ዳግመኛ ጠርተው፣ “አንተ ሰው፤ እግዚአብሔርን አክብር፤ ይህ ሰው ኀጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን” አሉት። እርሱም፣ “ኀጢአተኛ መሆኑን እኔ አላውቅም፤ ነገር ግን ዐይነ ስውር እንደ ነበርሁ፤ አሁን ግን እንደማይ ይህን አንድ ነገር ዐውቃለሁ!” አለ። እነርሱም፣ “ምን አደረገልህ? እንዴትስ ዐይንህን ከፈተ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “አስቀድሜ ነገርኋችሁ፤ አላዳመጣችሁኝም፤ ለምን እንደ ገና መስማት ፈለጋችሁ? እናንተም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትሻላችሁ?” አለ።
ዮሐንስ 9 ያንብቡ
ያዳምጡ ዮሐንስ 9
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዮሐንስ 9:6-27
9 ቀናት
እያንዳንዳቸው እየሱስ ክርስቶስ የህያው የእግዛብሔር ልጅ መሆኑን መልካም የምስራች ዜናን ያበስሩ ነበር። ይህ አጭር ቪዲዮ የኢሱስ ክርስቶስ የእያንዳንዱን ቀን ቁልፍ ተአምራትን በምሳሌ ይገልፃል።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች