ዮሐንስ 9:1-34

ዮሐንስ 9:1-34 NASV

በመንገድ ሲያልፍም ከተወለደ ጀምሮ ዐይነ ስውር የሆነ ሰው አየ። ደቀ መዛሙርቱም፣ “ረቢ፤ ይህ ሰው ዐይነ ስውር ሆኖ እንዲወለድ ኀጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ራሱ ወይስ ወላጆቹ?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እርሱ ወይም ወላጆቹ ኀጢአት አልሠሩም፤ ይህ የሆነው ግን የእግዚአብሔር ሥራ በርሱ ሕይወት እንዲገለጥ ነው። ቀን ሳለ፣ የላከኝን ሥራ መሥራት አለብን፤ ማንም ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ይመጣል፤ በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ።” ይህን ካለ በኋላ፣ በምድር ላይ እንትፍ ብሎ በምራቁ ጭቃ አበጀ፤ የሰውየውንም ዐይን ቀባና፣ “ሄደህ በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ” አለው፤ ሰሊሆም ማለት “የተላከ” ማለት ነው። ሰውየውም ሄዶ ታጠበ፤ እያየም ተመልሶ መጣ። ጎረቤቶቹና ከዚህ ቀደም ብሎ ሲለምን ያዩት ሰዎች፣ “ይህ ሰው ተቀምጦ ሲለምን የነበረው አይደለምን?” አሉ። አንዳንዶቹም፣ “በርግጥ እርሱ ነው” አሉ። ሌሎችም፣ “ይመስለዋል እንጂ እርሱ አይደለም” አሉ። እርሱ ግን፣ “እኔው ነኝ” አለ። እነርሱም፣ “ታዲያ ዐይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም፣ “ኢየሱስ የሚሉት ሰው ጭቃ አድርጎ ዐይኔን ቀባኝ፤ ወደ ሰሊሆም ሄጄ እንድታጠብም ነገረኝ፤ ሄጄ ታጠብሁ፤ ማየትም ቻልሁ” ሲል መለሰ። እነርሱም፣ “ታዲያ፣ ያ ሰው የት አለ?” አሉት። እርሱም፣ “እኔ አላውቅም” አለ። እነርሱም ዐይነ ስውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። ኢየሱስ ጭቃ የሠራበት፣ የሰውየውንም ዐይን የከፈተበት ቀን ሰንበት ነበር። ስለዚህ ፈሪሳውያንም እንዴት ማየት እንደ ቻለ ጠየቁት። ሰውየውም፣ “እርሱ ዐይኔን ጭቃ ቀባኝ፤ እኔም ታጠብሁ፤ ይኸው አያለሁ” አላቸው። ከፈሪሳውያንም አንዳንዶቹ፣ “ይህ ሰው ሰንበትን ስለማያከብር፣ ከእግዚአብሔር አይደለም” አሉ። ሌሎች ግን፣ “ኀጢአተኛ፣ እንዲህ ያሉትን ታምራዊ ምልክቶች እንዴት ሊያደርግ ይችላል?” አሉ። በመካከላቸውም አለመስማማት ተፈጠረ። ስለዚህ፣ ዐይነ ስውር ወደ ነበረው ሰው ተመልሰው፣ “ዐይንህን ስለ ከፈተው ሰው፣ እንግዲህ አንተ ምን ትላለህ?” አሉት። ሰውየውም፣ “እርሱ ነቢይ ነው” አለ። አይሁድ ወደ ወላጆቹ ልከው እስኪያስጠሯቸው ድረስ፣ ሰውየው ዐይነ ስውር እንደ ነበረና እንዳየ አላመኑም ነበር። እነርሱም፣ “ዐይነ ስውር ሆኖ ተወልዷል የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታዲያ አሁን እንዴት ሊያይ ቻለ?” አሏቸው። ወላጆቹም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ልጃችን መሆኑንና ዐይነ ስውር ሆኖ መወለዱን እናውቃለን፤ አሁን ግን እንዴት ማየት እንደ ቻለና ዐይኖቹን ማን እንደ ከፈተለት እኛ አናውቅም። ሙሉ ሰው ስለ ሆነ፣ ስለ ራሱ መናገር ይችላልና እርሱን ጠይቁት።” ኢየሱስን፣ ክርስቶስ ነው ብሎ የመሰከረ ሁሉ ከምኵራብ እንዲባረር አይሁድ አስቀድመው ወስነው ስለ ነበር፣ ወላጆቹ ይህን ያሉት አይሁድን ፈርተው ነው። ስለዚህ ወላጆቹ፣ “ሙሉ ሰው ስለ ሆነ እርሱን ጠይቁት” አሉ። ዐይነ ስውር የነበረውንም ሰው ዳግመኛ ጠርተው፣ “አንተ ሰው፤ እግዚአብሔርን አክብር፤ ይህ ሰው ኀጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን” አሉት። እርሱም፣ “ኀጢአተኛ መሆኑን እኔ አላውቅም፤ ነገር ግን ዐይነ ስውር እንደ ነበርሁ፤ አሁን ግን እንደማይ ይህን አንድ ነገር ዐውቃለሁ!” አለ። እነርሱም፣ “ምን አደረገልህ? እንዴትስ ዐይንህን ከፈተ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “አስቀድሜ ነገርኋችሁ፤ አላዳመጣችሁኝም፤ ለምን እንደ ገና መስማት ፈለጋችሁ? እናንተም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትሻላችሁ?” አለ። ከዚህ በኋላ በርሱ ላይ የስድብ ናዳ በማውረድ እንዲህ አሉት፤ “የዚህ ሰው ደቀ መዝሙር አንተ ነህ፤ እኛስ የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን! እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከየት እንደ መጣ እንኳ አናውቅም።” ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እናንተ ከየት እንደ መጣ አለማወቃችሁ የሚያስደንቅ ነው፤ ይሁን እንጂ እርሱ ዐይኖቼን ከፈተልኝ። እግዚአብሔር የሚሰማው፣ የሚፈራውንና ፈቃዱን የሚያደርገውን እንጂ፣ ኀጢአተኞችን እንደማይሰማ እናውቃለን፤ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደን ሰው ዐይን የከፈተ አለ ሲባል፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ማንም ሰምቶ አያውቅም። ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ይህን ማድረግ ባልቻለ ነበር።” እነርሱም፣ “ሁለንተናህ በኀጢአት ተነክሮ የተወለድህ፣ አንተ እኛን ለማስተማር እንዴት ትደፍራለህ?” ሲሉ መለሱለት፤ አባረሩትም።