በዚህ ጊዜ በኢየሩሳሌም የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ አሉ፤ “ሊገድሉት የሚፈልጉት ሰው ይህ አይደለምን? ይኸው እርሱ በአደባባይ ይናገራል፤ አንድም ቃል አይናገሩትም፤ ክርስቶስ ነው ብለው ባለሥልጣኖቹም ተቀብለውት ይሆን? ይህ ሰው ግን ከየት እንደ ሆነ እኛ እናውቃለን፤ ክርስቶስ ሲመጣ እኮ ከየት እንደ ሆነ ማንም አያውቅም።” ኢየሱስ በቤተ መቅደስ አደባባይ ሲያስተምር ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “አዎን፣ እኔን ታውቁኛላችሁ፤ ከየት እንደ ሆንሁም ታውቃላችሁ። እኔ እዚህ ያለሁት በገዛ ራሴ አይደለም፤ ነገር ግን የላከኝ እርሱ እውነተኛ ነው። እናንተ አታውቁትም፤ እኔ ግን ከርሱ ዘንድ ስለ ሆንሁ፣ እርሱም ስለ ላከኝ ዐውቀዋለሁ።” ስለዚህ ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን አላሳረፈበትም፤ ሆኖም ከሕዝቡ ብዙዎች በርሱ አምነው፣ “ታዲያ፣ ክርስቶስ ሲመጣ ይህ ሰው ከሚሠራቸው ታምራዊ ምልክቶች የበለጠ ያደርጋል?” አሉ። ፈሪሳውያን፣ ሕዝቡ ስለ እርሱ በጕምጕምታ የሚነጋገረውን ነገር ሰሙ፤ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም እንዲይዙት የቤተ መቅደስ ጠባቂዎችን ላኳቸው። ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ከእናንተ ጋራ የምቈየው ጥቂት ጊዜ ነው፤ ከዚያም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ፤ ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፤ እኔ ወዳለሁበትም ልትመጡ አትችሉም።” አይሁድም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “ይህ ሰው፣ ልናገኘው የማንችለው ወዴት ለመሄድ ቢያስብ ነው? በግሪኮች መካከል ተበታትነው ወደሚኖሩት ወገኖቻችን ሄዶ ግሪኮችን ሊያስተምር ፈልጎ ይሆን? ‘ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፤ እኔ ወዳለሁበትም ልትመጡ አትችሉም’ ሲል ምን ማለቱ ይሆን?” የበዓሉ መጨረሻ በሆነው በታላቁ ቀን፣ ኢየሱስ ቆሞ ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ አለ፤ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ፤ በእኔ የሚያምን፣ መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውሃ ምንጭ ከውስጡ ይፈልቃል።” ይህን ያለው በርሱ የሚያምኑ ስለሚቀበሉት መንፈስ ነበር፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ አልተሰጠም ነበር። ከሕዝቡ አንዳንዶቹ ቃሉን ሰምተው፣ “ይህ ሰው በርግጥ ነቢዩ ነው” አሉ። ሌሎችም፣ “እርሱ ክርስቶስ ነው” አሉ። ሌሎች ደግሞ እንዲህ አሉ፤ “ክርስቶስ ከገሊላ እንዴት ሊመጣ ይችላል? መጽሐፍ፣ ክርስቶስ ከዳዊት ዘር፣ ዳዊትም ከኖረበት ከቤተ ልሔም እንደሚመጣ ይናገር የለምን?” ስለዚህም በኢየሱስ ምክንያት በሕዝቡ መካከል መለያየት ሆነ፤ አንዳንዶቹም ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ማንም እጁን አላሳረፈበትም።
ዮሐንስ 7 ያንብቡ
ያዳምጡ ዮሐንስ 7
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዮሐንስ 7:25-44
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች