ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ጥብርያዶስ የተባለውን የገሊላ ባሕር ተሻግሮ ራቅ ወዳለው የባሕሩ ዳርቻ ሄደ። ብዙ ሰዎችም በሽተኞችን በመፈወስ ያደረጋቸውን ታምራዊ ምልክቶች ስላዩ ተከተሉት። ከዚያም ኢየሱስ ወደ ተራራ ወጥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ተቀመጠ። የአይሁድ የፋሲካ በዓልም ተቃርቦ ነበር። ኢየሱስም ቀና ብሎ ሲመለከት፣ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየ፤ ፊልጶስንም፣ “እነዚህ ሰዎች እንዲበሉ እንጀራ ከየት እንግዛ?” አለው። ይህን የጠየቀው ሊፈትነው እንጂ ራሱ ሊያደርግ ያሰበውን ያውቅ ነበር። ፊልጶስም፣ “እያንዳንዱ ሰው ትንሽ ትንሽ እንዲቃመስ ለማድረግ፣ የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ እንኳ አይበቃም” ሲል መለሰ። ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስም፣ እንዲህ አለ፤ “ዐምስት ትንንሽ የገብስ እንጀራና ሁለት ትንንሽ ዓሣ የያዘ አንድ ልጅ እዚህ አለ፤ ይህ ግን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ እንዴት ይዳረሳል?” ኢየሱስም፣ “ሰዎቹ እንዲቀመጡ አድርጉ” አለ። በዚያ ቦታ ብዙ ሣር ነበረ፤ ዐምስት ሺሕ ያህል ወንዶችም ተቀመጡ። ኢየሱስ ዐምስቱን እንጀራ አንሥቶ አመሰገነ፤ ለተቀመጡትም የሚፈልጉትን ያህል ዐደለ፤ ዓሣውንም እንዲሁ። ሁሉም በልተው ከጠገቡ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ከተረፈው ቍርስራሽ ምንም እንዳይባክን ሰብስቡ” አላቸው። እነርሱም፣ ከተበላው ዐምስት የገብስ እንጀራ የተረፈውን ቍርስራሽ ሰብስበው ዐሥራ ሁለት መሶብ ሞሉ። ሰዎቹም ኢየሱስ ያደረገውን ታምራዊ ምልክት ካዩ በኋላ፣ “ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ በርግጥ ይህ ነው” አሉ። ኢየሱስም ሰዎቹ መጥተው በግድ ሊያነግሡት እንዳሰቡ ዐውቆ እንደ ገና ብቻውን ወደ ተራራ ገለል አለ። በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕር ወረዱ፤ በጀልባውም ተሳፍረው ወደ ቅፍርናሆም ለመሻገር ተነሡ። ጊዜው መሽቶ ነበር፤ ኢየሱስም ወደ እነርሱ ገና አልመጣም ነበር። ኀይለኛ ነፋስ ይነፍስ ስለ ነበር ባሕሩ ተናወጠ። ዐምስት ወይም ስድስት ኪሎ ሜትር ያህል እንደ ቀዘፉ፣ ኢየሱስ በውሃ ላይ እየተራመደ ወደ ጀልባዋ ሲመጣ አይተው ፈሩ። እርሱ ግን፣ “እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” አላቸው። እነርሱም እንዲሳፈር ፈለጉ፤ ጀልባዋም ወዲያውኑ ወደሚሄዱበት ዳርቻ ደረሰች። በማግስቱም በባሕሩ ማዶ የቀሩት ሰዎች በዚያ አንዲት ጀልባ ብቻ እንደ ነበረች ተረዱ፤ ኢየሱስ እንዳልተሳፈረና ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን እንደ ሄዱም ዐወቁ። ከዚያም በኋላ፣ ሌሎች ጀልባዎች ከጥብርያዶስ ሕዝቡ ጌታ የባረከውን እንጀራ ወደ በላበት ስፍራ መጡ። ሰዎቹም፣ ኢየሱስ ወይም ደቀ መዛሙርቱ በዚያ አለመኖራቸውን እንዳወቁ፣ ኢየሱስን ፍለጋ በጀልባዎቹ ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ። ከባሕሩ ማዶ ባገኙትም ጊዜ፣ “ረቢ፤ መቼ ወደዚህ መጣህ?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ የምትፈልጉኝ እንጀራ ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ እንጂ፣ ታምራዊ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም። ለሚጠፋ እንጀራ አትሥሩ፤ ነገር ግን የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር ምግብ ሥሩ፤ ለዚህም እግዚአብሔር አብ ማረጋገጫ ማኅተሙን በርሱ ላይ ዐትሟልና።” እነርሱም፣ “ታዲያ የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ምን ማድረግ አለብን?” አሉት። ኢየሱስም፣ “እርሱ በላከው ታምኑ ዘንድ፣ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ ነው” ሲል መለሰላቸው። ስለዚህ እንዲህ ብለው ጠየቁት፤ “አይተን እንድናምንህ ምን ታምራዊ ምልክት ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ? ‘ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራን ሰጣቸው’ ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ።” ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ እውነተኛውን እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ ግን አባቴ ነው፤ የእግዚአብሔር እንጀራ፣ እርሱ ከሰማይ የሚወርድ፣ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና።” እነርሱም፣ “ጌታ ሆይ፤ እንግዲያውስ ይህን እንጀራ ሁልጊዜ ስጠን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔም የሚያምን ፈጽሞ አይጠማም። ነገር ግን እንደ ነገርኋችሁ፣ አይታችሁኝም እንኳ አታምኑም። አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም፤ ከሰማይ የወረድሁት የራሴን ፈቃድ ለማድረግ ሳይሆን፣ የላከኝን የርሱን ፈቃድ ለመፈጸም ነውና፤ የላከኝም ፈቃድ፣ ከሰጠኝ ሁሉ አንድ እንኳ ሳይጠፋብኝ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣ ነው። የአባቴ ፈቃድ ወልድን አይቶ በርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።”
ዮሐንስ 6 ያንብቡ
ያዳምጡ ዮሐንስ 6
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዮሐንስ 6:1-40
9 ቀናት
እያንዳንዳቸው እየሱስ ክርስቶስ የህያው የእግዛብሔር ልጅ መሆኑን መልካም የምስራች ዜናን ያበስሩ ነበር። ይህ አጭር ቪዲዮ የኢሱስ ክርስቶስ የእያንዳንዱን ቀን ቁልፍ ተአምራትን በምሳሌ ይገልፃል።
11 ቀናት
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልድ ሆኖ ከዘላለም ጀምሮ አለ። ኃጢአተኞችንም እንደገና በእግዚአብሔር ፊት ለማቅረብ ወደ ምድር መጣ። የጌታችን ኢየሱስ በማዳን ሥራው ውስጥ በሦስት ዋና ማንነቶቹ፤ እርሱም የመጨረሻውና የዘላለም ነቢይ፣ ካህን እና ንጉሥ መሆኑ ተገጿል። በዚህ የንባብ እቅድ ውስጥ እነዚህን ማንነቶቹን ለመረዳት 11 ቀናትን በመውሰድ እንመለከተዋለን።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች