ዮሐንስ 4:31-54

ዮሐንስ 4:31-54 NASV

በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ፣ “ረቢ፣ እህል ቅመስ እንጂ” አሉት። እርሱ ግን፣ “እናንተ የማታውቁት፣ የምበላው ምግብ አለኝ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም፣ “ሰው ምግብ አምጥቶለት ይሆን እንዴ?” ተባባሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው፤ እናንተ፣ ‘ከአራት ወር በኋላ መከር ይደርሳል’ ትሉ የለምን? እነሆ፣ አዝመራው ለመከር እንደ ደረሰ ቀና ብላችሁ ማሳውን ተመልከቱ እላችኋለሁ። ዐጫጁ አሁንም ቢሆን እንኳ ደመወዙን እየተቀበለ ነው፤ ለዘላለም ሕይወት ይሆን ዘንድ አዝመራውን ይሰበስባል፤ ይህም ዘሪውና ዐጫጁ በጋራ ደስ እንዲላቸው ነው። ስለዚህ፣ ‘አንዱ ይዘራል፤ ሌላውም ያጭዳል’ የተባለው ምሳሌ እውነት ነው። ያልደከማችሁበትን እንድታጭዱ ላክኋችሁ፤ አድካሚውን ሥራ ሌሎች ሠሩ፤ እናንተም የድካማቸውን ፍሬ ሰበሰባችሁ።” ሴቲቱም፣ “ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ” ብላ ስለ መሰከረች፣ ከዚያች ከተማ ብዙ ሳምራውያን በርሱ አመኑ። ስለዚህ፣ ሳምራውያኑ ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ ዐብሯቸው እንዲቈይ አጥብቀው ለመኑት፤ እዚያም ሁለት ቀን ቈየ። ከቃሉም የተነሣ ሌሎች ብዙዎች አመኑ። ሴትዮዋንም፣ “ከእንግዲህ የምናምነው አንቺ ስለ ነገርሽን ብቻ አይደለም፤ እኛ ራሳችን ሰምተነዋል፤ ይህ ሰው በእውነት የዓለም አዳኝ እንደ ሆነ እናውቃለን” አሏት። ከሁለቱ ቀናት በኋላም ወደ ገሊላ ሄደ፤ ነቢይ በገዛ አገሩ እንደማይከበር ኢየሱስ ራሱ ተናግሮ ነበርና። ገሊላ እንደ ደረሰም የገሊላ ሰዎች በደስታ ተቀበሉት፤ ምክንያቱም፣ እነርሱም በፋሲካ በዓል ኢየሩሳሌም ስለ ነበሩና በዚያ ያደረገውን ሁሉ ስላዩ ነው። ኢየሱስም ውሃውን የወይን ጠጅ ወዳደረገበት፣ በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ቃና ከተማ ዳግመኛ መጣ፤ በቅፍርናሆምም ልጁ የታመመበት አንድ የቤተ መንግሥት ሹም ነበረ፤ ይህም ሰው ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መምጣቱን በሰማ ጊዜ፣ ወደ እርሱ ሄደና በሞት አፋፍ ላይ የነበረውን ልጁን መጥቶ እንዲፈውስለት ለመነው። ኢየሱስም፣ “መቼውንም እናንተ ምልክቶችንና ድንቅ ነገሮችን ካላያችሁ አታምኑም” አለው። ሹሙም፣ “ጌታዬ፤ ልጄ ከመሞቱ በፊት እባክህ ድረስልኝ” አለው። ኢየሱስም፣ “ልጅህ በሕይወት ይኖራልና ሂድ” አለው። ሰውየውም ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አምኖ ሄደ፤ በመንገድ ላይ እንዳለም፣ ባሮቹ አግኝተውት ልጁ በሕይወት መኖሩን ነገሩት። እርሱም ልጁ በስንት ሰዓት እንደ ተሻለው ሲጠይቃቸው፣ “ትኵሳቱ የለቀቀው ትናንት በሰባት ሰዓት ላይ ነው” አሉት። አባትየውም ሰዓቱ ኢየሱስ፣ “ልጅህ በሕይወት ይኖራል” ያለበት ሰዓት መሆኑን ተገነዘበ፤ እርሱና ቤተ ሰቡም ሁሉ አመኑ። ይህም፣ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛው ታምራዊ ምልክት ነው።