ዮሐንስ 4:1-53

ዮሐንስ 4:1-53 NASV

ፈሪሳውያን ከዮሐንስ ይልቅ ኢየሱስ ብዙ ደቀ መዛሙርትን እንዳፈራና እንዳጠመቀ ሰሙ፤ ዳሩ ግን ያጠመቀው ኢየሱስ ሳይሆን ደቀ መዛሙርቱ ነበሩ። ጌታም ይህን እንዳወቀ ይሁዳን ለቅቆ ወደ ገሊላ ተመልሶ ሄደ። በሰማርያም በኩል ማለፍ ነበረበት። ስለዚህ በሰማርያ፣ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ቦታ አጠገብ ወደ ነበረች፣ ሲካር ወደምትባል ከተማ መጣ። በዚያም የያዕቆብ የውሃ ጕድጓድ ነበረ፤ ኢየሱስም ከጕዞው የተነሣ ደክሞት ስለ ነበር በውሃው ጕድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ከቀኑ ስድስት ሰዓት አካባቢ ነበር። አንዲት ሳምራዊት ሴት ውሃ ለመቅዳት ስትመጣ ኢየሱስ፣ “እባክሽ የምጠጣው ስጪኝ” አላት፤ ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ለመግዛት ወደ ከተማ ሄደው ነበር። ሳምራዊቷም፣ “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ፣ እኔን ሳምራዊቷን እንዴት ውሃ አጠጪኝ ትላለህ?” አለችው፤ ይህን ማለቷ አይሁድ ከሳምራውያን ጋራ ስለማይተባበሩ ነው። ኢየሱስም፣ “የእግዚአብሔርን ስጦታ ብታውቂና ውሃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑን ብትረጂ ኖሮ፣ አንቺው በጠየቅሽው፣ እርሱም የሕይወትን ውሃ በሰጠሽ ነበር” ሲል መለሰላት። ሴትዮዋም እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ፣ መቅጃ የለህም፤ ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ ታዲያ ይህን የሕይወት ውሃ ከየት ታገኛለህ? ለመሆኑ አንተ፣ ይህን ጕድጓድ ከሰጠን፣ ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? እርሱ ራሱና ልጆቹ፣ እንስሳቱም ከዚሁ ጕድጓድ ጠጥተዋል።” ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላት፤ “ከዚህ ውሃ የሚጠጣ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ግን ከቶ አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት ውሃ ምንጭ ይሆናል።” ሴትዮዋም፣ “ጌታዬ፤ እንዳልጠማና ውሃ ለመቅዳት እንዳልመላለስ፣ እባክህ ይህን ውሃ ስጠኝ” አለችው። እርሱም፣ “ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ተመለሽ” አላት። ሴትዮዋም፣ “ባል የለኝም” ብላ መለሰች። ኢየሱስም፣ እንዲህ አላት፤ “ባል የለኝም ማለትሽ ትክክል ነው፤ በርግጥ ዐምስት ባሎች ነበሩሽ፤ አሁን ከአንቺ ጋራ ያለውም ባልሽ ስላልሆነ፣ የተናገርሽው እውነት ነው።” ሴትዮዋም እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ፣ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ፤ አባቶቻችን በዚህ ተራራ ላይ ሰገዱ፤ እናንተ አይሁድ ግን ሰው መስገድ ያለበት በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ” አለችው። ኢየሱስም እንዲህ አላት፤ “አንቺ ሴት፤ በዚህ ተራራም ሆነ በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ እንደሚመጣ እመኚኝ። እናንተ ሳምራውያን ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ ግን ድነት ከአይሁድ ስለ ሆነ ለምናውቀው እንሰግዳለን። በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቷል፤ አብም እንደዚህ በእውነት የሚሰግዱለትን ይፈልጋል። እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል።” ሴትዮዋም፣ “ክርስቶስ የተባለ መሲሕ እንደሚመጣ ዐውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ነገር ይነግረናል” አለችው። ኢየሱስም፣ “የማነጋግርሽ እኮ እኔ እርሱ ነኝ” ሲል ገልጾ ነገራት። በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው መጡ፤ ከሴት ጋራ ሲነጋገር በማግኘታቸው ተደነቁ፤ ሆኖም ግን፤ “ምን ፈለግህ?” ወይም፣ “ከርሷ ጋራ የምትነጋገረው ለምንድን ነው?” ብሎ የጠየቀው ማንም አልነበረም። ሴትዮዋም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ተመለሰች፤ ለሕዝቡም፣ “ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እርሱ ክርስቶስ ይሆን እንዴ?” አለች፤ እነርሱም ከከተማ ወጥተው እርሱ ወዳለበት አመሩ። በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ፣ “ረቢ፣ እህል ቅመስ እንጂ” አሉት። እርሱ ግን፣ “እናንተ የማታውቁት፣ የምበላው ምግብ አለኝ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም፣ “ሰው ምግብ አምጥቶለት ይሆን እንዴ?” ተባባሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው፤ እናንተ፣ ‘ከአራት ወር በኋላ መከር ይደርሳል’ ትሉ የለምን? እነሆ፣ አዝመራው ለመከር እንደ ደረሰ ቀና ብላችሁ ማሳውን ተመልከቱ እላችኋለሁ። ዐጫጁ አሁንም ቢሆን እንኳ ደመወዙን እየተቀበለ ነው፤ ለዘላለም ሕይወት ይሆን ዘንድ አዝመራውን ይሰበስባል፤ ይህም ዘሪውና ዐጫጁ በጋራ ደስ እንዲላቸው ነው። ስለዚህ፣ ‘አንዱ ይዘራል፤ ሌላውም ያጭዳል’ የተባለው ምሳሌ እውነት ነው። ያልደከማችሁበትን እንድታጭዱ ላክኋችሁ፤ አድካሚውን ሥራ ሌሎች ሠሩ፤ እናንተም የድካማቸውን ፍሬ ሰበሰባችሁ።” ሴቲቱም፣ “ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ” ብላ ስለ መሰከረች፣ ከዚያች ከተማ ብዙ ሳምራውያን በርሱ አመኑ። ስለዚህ፣ ሳምራውያኑ ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ ዐብሯቸው እንዲቈይ አጥብቀው ለመኑት፤ እዚያም ሁለት ቀን ቈየ። ከቃሉም የተነሣ ሌሎች ብዙዎች አመኑ። ሴትዮዋንም፣ “ከእንግዲህ የምናምነው አንቺ ስለ ነገርሽን ብቻ አይደለም፤ እኛ ራሳችን ሰምተነዋል፤ ይህ ሰው በእውነት የዓለም አዳኝ እንደ ሆነ እናውቃለን” አሏት። ከሁለቱ ቀናት በኋላም ወደ ገሊላ ሄደ፤ ነቢይ በገዛ አገሩ እንደማይከበር ኢየሱስ ራሱ ተናግሮ ነበርና። ገሊላ እንደ ደረሰም የገሊላ ሰዎች በደስታ ተቀበሉት፤ ምክንያቱም፣ እነርሱም በፋሲካ በዓል ኢየሩሳሌም ስለ ነበሩና በዚያ ያደረገውን ሁሉ ስላዩ ነው። ኢየሱስም ውሃውን የወይን ጠጅ ወዳደረገበት፣ በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ቃና ከተማ ዳግመኛ መጣ፤ በቅፍርናሆምም ልጁ የታመመበት አንድ የቤተ መንግሥት ሹም ነበረ፤ ይህም ሰው ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መምጣቱን በሰማ ጊዜ፣ ወደ እርሱ ሄደና በሞት አፋፍ ላይ የነበረውን ልጁን መጥቶ እንዲፈውስለት ለመነው። ኢየሱስም፣ “መቼውንም እናንተ ምልክቶችንና ድንቅ ነገሮችን ካላያችሁ አታምኑም” አለው። ሹሙም፣ “ጌታዬ፤ ልጄ ከመሞቱ በፊት እባክህ ድረስልኝ” አለው። ኢየሱስም፣ “ልጅህ በሕይወት ይኖራልና ሂድ” አለው። ሰውየውም ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አምኖ ሄደ፤ በመንገድ ላይ እንዳለም፣ ባሮቹ አግኝተውት ልጁ በሕይወት መኖሩን ነገሩት። እርሱም ልጁ በስንት ሰዓት እንደ ተሻለው ሲጠይቃቸው፣ “ትኵሳቱ የለቀቀው ትናንት በሰባት ሰዓት ላይ ነው” አሉት። አባትየውም ሰዓቱ ኢየሱስ፣ “ልጅህ በሕይወት ይኖራል” ያለበት ሰዓት መሆኑን ተገነዘበ፤ እርሱና ቤተ ሰቡም ሁሉ አመኑ።