ከዚያም በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር እንደ ገና ለደቀ መዛሙርቱ ታየ፤ በዚህም ሁኔታ ተገለጠ፤ ስምዖን ጴጥሮስ፣ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፣ የቃና ዘገሊላው ናትናኤል፣ የዘብዴዎስ ልጆችና ከደቀ መዛሙርቱ ሌሎች ሁለት አንድ ላይ ነበሩ። ስምዖን ጴጥሮስም፣ “ዓሣ ላጠምድ መሄዴ ነው” አላቸው፤ እነርሱም፣ “እኛም ከአንተ ጋራ እንሄዳለን” አሉት። ወጥተውም ወደ ጀልባዋ ገቡ፤ በዚያ ሌሊት ግን ምንም አላጠመዱም። ሲነጋም፣ ኢየሱስ በባሕሩ ዳርቻ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም ነበር። እርሱም፣ “ልጆች፣ ዓሣ አላችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “የለንም” አሉት። እርሱም፣ “መረባችሁን ከጀልባው በስተቀኝ ጣሉ፤ ዓሣ ታገኛላችሁ” አላቸው። እነርሱም በጣሉ ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ መረቡን መጐተት አቃታቸው። ኢየሱስ ይወድደው የነበረው ደቀ መዝሙርም፣ ጴጥሮስን፣ “ጌታ እኮ ነው!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም፣ “ጌታ እኮ ነው!” የሚለውን ቃል በሰማ ጊዜ፣ አውልቆት የነበረውን መደረቢያ ልብስ ታጠቀና ዘልሎ ወደ ባሕሩ ገባ። ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን ከባሕሩ ዳርቻ የራቁት ሁለት መቶ ክንድ ያህል ብቻ ስለ ነበር፣ ዓሣ የሞላበትን መረብ እየሳቡ በጀልባዋ መጡ። ወደ ምድርም በደረሱ ጊዜ፣ ዓሣ በላዩ የነበረበት የከሰል ፍምና እንጀራ አዩ። ኢየሱስም፣ “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ እስኪ አምጡ” አላቸው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ወደ ጀልባዋ ወጥቶ መረቡን ወደ ምድር ጐተተው፤ መረቡንም መቶ ዐምሳ ሦስት ትልልቅ ዓሣ ሞልተውት ነበር፤ ይህን ያህል ቢይዝም መረቡ አልተቀደደም። ኢየሱስም “ኑ፤ ቍርስ ብሉ” አላቸው። ጌታ እንደ ሆነ ዐውቀው ስለ ነበር፣ ከደቀ መዛሙርቱ፣ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ለመጠየቅ የደፈረ አልነበረም። ኢየሱስም መጥቶ እንጀራውን አንሥቶ ሰጣቸው፤ እንዲሁም ዓሣውን ሰጣቸው። እንግዲህ ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲታይ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው። በልተው ካበቁ በኋላ፣ ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፣ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፤ ከእነዚህ አብልጠህ ትወድደኛለህን?” አለው። እርሱም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም፣ “ጠቦቶቼን መግብ” አለው። ኢየሱስም ለሁለተኛ ጊዜ፣ “የዮና ልጅ፣ ስምዖን ሆይ፤ በእውነት ትወድደኛለህን?” አለው። እርሱም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም፣ “በጎቼን ጠብቅ” አለው። ሦስተኛም ጊዜ፣ “የዮና ልጅ፣ ስምዖን ሆይ፤ ትወድደኛለህን?” አለው። ጴጥሮስም ሦስተኛ ጊዜ ኢየሱስ፣ “ትወድደኛለህን?” ብሎ ስለ ጠየቀው ዐዝኖ፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንደምወድድህም ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “በጎቼን መግብ።
ዮሐንስ 21 ያንብቡ
ያዳምጡ ዮሐንስ 21
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዮሐንስ 21:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች