በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን፣ በማለዳ ገና ጨለማ ሳለ፣ መግደላዊት ማርያም ወደ መቃብሩ ሄደች፤ ድንጋዩም ከመቃብሩ ተንከባልሎ አየች። ስለዚህም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወድደው ወደ ነበረው ሌላው ደቀ መዝሙር እየሮጠች መጥታ፣ “ጌታን ከመቃብር አውጥተው ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አናውቅም!” አለቻቸው። ከዚያም ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ሁለቱም ይሮጡ ነበር፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ጴጥሮስን ቀድሞት ከመቃብሩ ደረሰ። ጐንበስ ብሎ ወደ ውስጥ ሲመለከት፣ በፍታውን ብቻ ተቀምጦ አየ፤ ወደ መቃብሩ ግን አልገባም። ይከተለው የነበረው ስምዖን ጴጥሮስ ደረሰና ወደ መቃብሩ ገባ፤ እርሱም ከተልባ እግር የተሠራውን ከፈን አየ፤ እንዲሁም በኢየሱስ ራስ ላይ ተጠምጥሞ የነበረውን ጨርቅ አየ፤ ይህም ጨርቅ ከከፈኑ ተለይቶ እንደ ተጠቀለለ ነበር። ከዚያም አስቀድሞ ከመቃብሩ የደረሰው ሌላው ደቀ መዝሙር ወደ ውስጥ ገባ፤ አይቶም አመነ፤ ይኸውም ኢየሱስ ከሙታን መነሣት እንዳለበት ገና ከመጽሐፍ ስላልተረዱ ነበር። ከዚያም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው ወደ የቤታቸው ሄዱ። ማርያም ግን ከመቃብሩ ውጭ ቆማ ታለቅስ ነበር፤ እያለቀሰችም መቃብሩን ለማየት ጐንበስ አለች። የኢየሱስ ሥጋ በነበረበት ቦታ፣ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክት አንዱ በራስጌ ሌላው በግርጌ ተቀምጠው አየች። እነርሱም፣ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ?” ብለው ጠየቋት። እርሷም፣ “ጌታዬን ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አላውቅም” አለች። ይህን ብላ ዘወር ስትል ኢየሱስ በዚያው ቆሞ አየች፤ ኢየሱስ መሆኑን ግን አላወቀችም። እርሱም፣ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊአለሽ?” አላት። እርሷም የአትክልቱ ቦታ ጠባቂ መስሏት፣ “ጌታዬ፤ አንተ ወስደኸው ከሆነ፣ እባክህ እንድወስደው፣ የት እንዳኖርኸው ንገረኝ” አለችው። ኢየሱስም፣ “ማርያም” አላት። እርሷም፣ ወደ እርሱ ዘወር ብላ በአራማይክ ቋንቋ፣ “ረቡኒ!” አለችው፤ ትርጕሙም “መምህር ሆይ” ማለት ነው። ኢየሱስም፣ “ገና ወደ አብ ስላላረግሁ፣ አትንኪኝ፤ ይልቁንስ ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፣ ‘ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ’ ብሏል ብለሽ ንገሪአቸው” አላት። መግደላዊት ማርያምም፣ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥታ፣ “ጌታን እኮ አየሁት!” አለች፤ እርሱ ያላትንም ነገረቻቸው።
ዮሐንስ 20 ያንብቡ
ያዳምጡ ዮሐንስ 20
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዮሐንስ 20:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች