ዮሐንስ 17:1-11

ዮሐንስ 17:1-11 NASV

ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ፣ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “አባት ሆይ፤ ጊዜው ደርሷል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው፤ ከአንተ ለተቀበላቸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት እንዲሰጥ፣ በሰው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥተኸዋልና። እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት። የሰጠኸኝን ሥራ በመፈጸም በምድር አከበርሁህ። እንግዲህ አባት ሆይ፤ ዓለም ሳይፈጠር ከአንተ ጋራ በነበረኝ ክብር በአንተ ዘንድ አክብረኝ። “ለእነዚህ ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ። የአንተ ነበሩ ለእኔ ሰጠኸኝ፤ እነርሱም ቃልህን ጠብቀዋል። የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ አሁን ዐውቀዋል፤ ምክንያቱም የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸው ተቀብለዋል፤ እኔም ከአንተ እንደ ወጣሁ በርግጥ ዐውቀዋል፤ አንተ እንደ ላክኸኝም አምነዋል፤ እነርሱ የአንተ ስለ ሆኑ እጸልይላቸዋለሁ፤ ለሰጠኸኝና የአንተ ለሆኑት እንጂ ለዓለም አልጸልይም። የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተ የሆነውም ሁሉ የእኔ ነው፤ በእነርሱም ከብሬአለሁ። ከእንግዲህ እኔ በዓለም አልቈይም፤ እነርሱ ግን በዓለም ውስጥ ናቸው፤ እኔም ወደ አንተ መምጣቴ ነው። ቅዱስ አባት ሆይ፤ እኛ አንድ እንደ ሆንን፣ እነርሱም አንድ እንዲሆኑ በሰጠኸኝ በስምህ ጠብቃቸው።