ዮሐንስ 16:17-33

ዮሐንስ 16:17-33 NASV

ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ፣ “  ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ’ እንዲሁም፣ ‘ወደ አብ ስለምሄድ’ ሲል ምን ማለቱ ነው?” ተባባሉ፤ “  ‘ጥቂት ጊዜ’ ማለቱስ ምን ይሆን? የሚለውም ነገር አልገባንም” እያሉ ይጠያየቁ ነበር። ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደ ፈለጉ ባወቀ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ፣ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ’ ስላልኋችሁ፣ ምን ማለቴ እንደ ሆነ እርስ በርሳችሁ ትጠያየቃላችሁ? እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ታዝናላችሁም፤ ዓለም ግን ሐሤት ያደርጋል፤ ይሁን እንጂ ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል። ሴት ቀኗ ደርሶ ስትወልድ ትጨነቃለች፤ ከተገላገለች በኋላ ግን፣ ሰው ወደ ዓለም ተወልዷልና ስለ ደስታዋ ጭንቋን ትረሳለች፤ ለእናንተም እንደዚሁ አሁን የሐዘን ጊዜ ነው፤ ሆኖም እንደ ገና አያችኋለሁ፤ ልባችሁም ደስ ይለዋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም። በዚያ ቀን ከእኔ ምንም አትለምኑም፤ እውነት እላችኋለሁ፤ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ለምኑ ትቀበላላችሁ፤ ደስታችሁም ሙሉ ይሆናል። “እስከ አሁን የነገርኋችሁ በምሳሌ ቢሆንም እንኳ፣ ከእንግዲህ ግን ስለ አብ በምሳሌ ሳይሆን በግልጽ የምናገርበት ጊዜ ይመጣል። በዚያ ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ ይህም በእናንተ ፈንታ አብን እለምናለሁ ማለቴ አይደለም፤ ስለ ወደዳችሁኝና ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ ራሱ ይወድዳችኋል። ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ አሁን ግን ዓለምን ትቼ ወደ አብ እሄዳለሁ።” ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አሉ፤ “አሁንም እኮ ያለ ምሳሌ በግልጽ እየተናገርህ ነው። አሁን ሁሉን ነገር እንደምታውቅና ማንም ሊጠይቅህ እንደማያስፈልግ ተረድተናል፤ ይህም ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እንድናምን አድርጎናል።” ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንስ አመናችሁ ማለት ነው? እነሆ፤ ሁላችሁም በየፊናችሁ የምትበታተኑበት ጊዜ ይመጣል፤ ያም ጊዜ አሁን ነው። እኔንም ብቻዬን ትተዉኛላችሁ፤ ይሁን እንጂ አባቴ ከእኔ ጋራ ስለ ሆነ ብቻዬን አይደለሁም። “በእኔ ሰላም እንዲኖራችሁ፣ ይህን ነግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”