ፊልጶስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አንተ ፊልጶስ! ይህን ያህል ጊዜ ከእናንተ ጋራ ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቷል፤ እንዴትስ፣ ‘አብን አሳየን’ ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ፣ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? የምነግራችሁ ቃል ከራሴ አይደለም፤ ነገር ግን ሥራውን የሚሠራው በእኔ የሚኖረው አብ ነው። እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ ስነግራችሁ እመኑኝ፤ ሌላው ቢቀር ስለ ድንቅ ሥራዎቹ እንኳ እመኑ። እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ ይሠራል፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ፣ ከእነዚህም የሚበልጥ ያደርጋል። አብ በወልድ እንዲከብር፣ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ፤ ማንኛውንም ነገር በስሜ ብትለምኑኝ፣ እኔ አደርገዋለሁ። “ብትወድዱኝ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ። እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋራ ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም የእውነት መንፈስ ነው፤ ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም። እናንተ ግን፣ ዐብሯችሁ ስለሚኖርና በውስጣችሁ ስለሚሆን ታውቁታላችሁ። ወላጅ እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ዓለም ከቶ አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ። እኔ ሕያው ስለ ሆንሁ እናንተም ሕያዋን ትሆናላችሁ። እኔ በአባቴ እንዳለሁ፣ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ፣ እኔም ደግሞ በእናንተ እንዳለሁ በዚያ ቀን ትረዳላችሁ። የሚወድደኝ ትእዛዜን ተቀብሎ የሚጠብቅ ነው፤ የሚወድደኝንም አባቴ ይወድደዋል፤ እኔም እወድደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ።” ከዚያም የአስቆሮቱ ያልሆነው ይሁዳ፣ “ጌታ ሆይ፤ ታዲያ፣ ለዓለም ሳይሆን ራስህን ለእኛ የምትገልጠው እንዴት ነው?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “የሚወድደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወድደዋል፤ ወደ እርሱ እንመጣለን፤ ከርሱም ጋራ እንኖራለን። የማይወድደኝ ቃሌን አይጠብቅም። ይህ የምትሰሙት ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም። “አሁን ከእናንተ ጋራ እያለሁ ይህን ሁሉ ነግሬአችኋለሁ፤ አብ በስሜ የሚልከው አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ግን ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል። ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም። ልባችሁ አይጨነቅ፤ አይፍራም። “ ‘እሄዳለሁ፤ ተመልሼም ወደ እናንተ እመጣለሁ’ ማለቴን ሰምታችኋል፤ ብትወድዱኝስ አብ ከእኔ ስለሚበልጥ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር፤ የተናገርሁት ሲፈጸም እንድታምኑ፣ ከመሆኑ በፊት አሁን ነግሬአችኋለሁ። የዚህ ዓለም ገዥ ስለሚመጣ ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋራ ብዙ አልናገርም። እርሱም በእኔ ላይ ሥልጣን የለውም፤ ነገር ግን እኔ አብን እንደምወድድ፣ አባቴ ያዘዘኝንም እንደማደርግ ዓለም እንዲያውቅ ነው። “ተነሡ፤ ከዚህ እንሂድ።
ዮሐንስ 14 ያንብቡ
ያዳምጡ ዮሐንስ 14
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዮሐንስ 14:8-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች