ይህን ካለ በኋላም ኢየሱስ በመንፈሱ ታውኮ፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” ሲል መሰከረ። ደቀ መዛሙርቱም ማንን ማለቱ እንደ ሆነ ግራ ተጋብተው እርስ በርሳቸው ተያዩ። ከእነርሱ አንዱ፣ ኢየሱስ ይወድደው የነበረ ደቀ መዝሙር ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ ተቀምጦ ነበር። ስምዖን ጴጥሮስም ይህን ደቀ መዝሙር በምልክት ጠቅሶ፣ “ማንን ማለቱ እንደ ሆነ ጠይቀው” አለው። እርሱም ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ፣ “ጌታ ሆይ፤ ማን ይሆን?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “ይህን ቍራሽ እንጀራ ከወጭቱ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው” አለው፤ ከዚያም ቍራሹን እንጀራ አጥቅሶ ለስምዖን ልጅ ለአስቆሮቱ ይሁዳ ሰጠው። ይሁዳም ቍራሹን እንጀራ እንደ ተቀበለ ወዲያው ሰይጣን ገባበት። ኢየሱስም፣ “የምታደርገውን ቶሎ አድርግ” አለው፤ ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለምን እንዲህ እንዳለው ማንም አላወቀም ነበረ። ይሁዳ ገንዘብ ያዥ ስለ ነበር፣ አንዳንዶቹ ለበዓሉ የሚያስፈልግ ነገር እንዲገዛ ወይም ለድኾች እንዲሰጥ ኢየሱስ የተናገረው መሰላቸው። ይሁዳም ያን ቍራሽ እንጀራ እንደ ተቀበለ ወጥቶ ሄደ፤ ሌሊትም ነበረ። ይሁዳ ከወጣ በኋላ፣ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “አሁን የሰው ልጅ ከበረ፤ በርሱም እግዚአብሔር ከበረ። እንግዲህ እግዚአብሔር በርሱ ከከበረ፣ እግዚአብሔር ልጁን በራሱ ዘንድ ያከብረዋል፤ ወዲያውም ያከብረዋል። “ልጆቼ ሆይ፤ ከእናንተ ጋራ የምቈየው ለጥቂት ጊዜ ነው፤ እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድ፣ ‘እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም’ እንዳልኋቸው፣ አሁንም ለእናንተ ይህንኑ እላችኋለሁ። “አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ ይኸውም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እንግዲህ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።” ስምዖን ጴጥሮስ፣ “ጌታ ሆይ፤ የምትሄደው ወዴት ነው?” አለው። ኢየሱስም፣ “ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፤ ኋላ ግን ትከተለኛለህ” ሲል መለሰለት። ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አሁን ልከተልህ የማልችለው ለምንድን ነው? ስለ አንተ ሕይወቴንም ቢሆን አሳልፌ እሰጣለሁ” አለው። ኢየሱስም፣ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሕይወትህን በርግጥ ለእኔ አሳልፈህ ትሰጣለህን? እውነት እልሃለሁ፤ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ።
ዮሐንስ 13 ያንብቡ
ያዳምጡ ዮሐንስ 13
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዮሐንስ 13:21-38
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች