ዮሐንስ 12:12-19

ዮሐንስ 12:12-19 NASV

በማግስቱም ለበዓሉ የመጣው ብዙ ሕዝብ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየመጣ መሆኑን ሰሙ፤ የዘንባባም ዝንጣፊ ይዘው ሊቀበሉት ወጡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፤ “ሆሳዕና!” “በጌታ ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው!” “የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው!” ኢየሱስም የአህያ ውርንጫ አግኝቶ ተቀመጠበት፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ “የጽዮን ልጅ ሆይ፤ አትፍሪ፤ እነሆ፤ ንጉሥሽ በአህያ ግልገል ተቀምጦ ይመጣል።” ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሁሉ በመጀመሪያ አላስተዋሉም፤ ስለ እርሱ የተጻፉትንና ለርሱም የተደረጉትን ልብ ያሉት ኢየሱስ ከከበረ በኋላ ነበር። አልዓዛርን ከመቃብር ጠርቶ ከሙታን ባስነሣበት ጊዜ፣ ከርሱ ጋራ የነበሩ ሰዎች መነሣቱን ይመሰክሩ ነበር። ብዙ ሰዎችም ይህን ታምራዊ ምልክት ማድረጉን ስለ ሰሙ ሊቀበሉት ወጡ። ስለዚህም ፈሪሳውያን እርስ በርሳቸው፣ “እንግዲህ ምን ማድረግ ይቻላል? አያችሁ፣ ዓለሙ ሁሉ ግልብጥ ብሎ ተከትሎታል!” ተባባሉ።