ዮሐንስ 12:1-11

ዮሐንስ 12:1-11 NASV

የፋሲካ በዓል ስድስት ቀን ሲቀረው፣ ኢየሱስ ከሞት ያስነሣው አልዓዛር ወደሚኖርበት፣ ወደ ቢታንያ መጣ። በዚያም ለኢየሱስ ሲባል እራት ተዘጋጀ። ማርታ ስታገለግል፣ አልዓዛር ከርሱ ጋራ በማእድ ከተቀመጡት አንዱ ነበር። ማርያምም ዋጋው ውድ የሆነ፣ ግማሽ ሊትር ንጹሕ የናርዶስ ሽቱ አምጥታ የኢየሱስን እግሮች ቀባች፤ እግሮቹንም በጠጕሯ አበሰች፤ ቤቱንም የሽቱው መዐዛ ሞላው። ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ ኋላ አሳልፎ የሚሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ግን በመቃወም እንዲህ አለ፤ “ይህ ሽቱ በሦስት መቶ ዲናር ተሸጦ ገንዘቡ ለድኾች ለምን አልተሰጠም?” ይህን የተናገረው የገንዘብ ከረጢት ያዥ በመሆኑ፣ ከሚቀመጠው ለራሱ የሚጠቀም ሌባ ስለ ነበር እንጂ ለድኾች ተቈርቍሮ አልነበረም። ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ይህ ሽቱ ለቀብሬ ቀን የታሰበ ስለ ሆነ እንድታቈየው ተዋት፤ ድኾች ምን ጊዜም ከእናንተ ጋራ ናቸው፤ እኔን ግን ሁልጊዜ አታገኙኝም።” በዚህ ጊዜ ብዙ አይሁድ ኢየሱስ በዚያ መኖሩን ዐውቀው መጡ፤ የመጡትም ኢየሱስን ብለው ብቻ ሳይሆን፣ እርሱ ከሙታን ያስነሣውን አልዓዛርንም ለማየት ነበር። ስለዚህ የካህናት አለቆች አልዓዛርን ጭምር ለመግደል ተማከሩ፤ ይህም በርሱ ምክንያት ብዙ አይሁድ ወደ ኢየሱስ እየሄዱ ያምኑበት ስለ ነበር ነው።