ኢየሱስ ሲደርስ አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት ነበር። ቢታንያ ከኢየሩሳሌም ዐሥራ ዐምስት ምዕራፍ ያህል ትርቅ ነበር። ብዙዎች አይሁድም ማርታንና ማርያምን ስለ ወንድማቸው ሞት ሊያጽናኗቸው መጥተው ነበር፤ ማርታ የኢየሱስን መምጣት ሰምታ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ቀርታ ነበር። ማርታም ኢየሱስን እንዲህ አለችው፤ “ጌታ ሆይ፤ አንተ በዚህ ብትሆን ኖሮ፣ ወንድሜ ባልሞተ ነበር። አሁንም ቢሆን የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ ዐውቃለሁ።” ኢየሱስም፣ “ወንድምሽ ይነሣል” አላት። ማርታም፣ “በመጨረሻው ቀን፣ በትንሣኤ እንደሚነሣ ዐውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም እንዲህ አላት፤ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል፤ በእኔ የሚኖር፣ የሚያምንብኝም ከቶ አይሞትም፤ ይህን ታምኛለሽን?” እርሷም፣ “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አምናለሁ” አለችው። ይህን ካለች በኋላ፣ ተመልሳ እኅቷን ማርያምን ለብቻዋ ጠርታ፣ “መምህሩ መጥቷል፤ ይፈልግሻልም” አለቻት። ማርያምም ይህን እንደ ሰማች፣ ፈጥና ተነሥታ ወደ እርሱ ሄደች። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ ማርታ እርሱን በተቀበለችበት ቦታ ነበር እንጂ፣ ገና ወደ መንደር አልገባም ነበር። ማርያምን ሲያጽናኑ በቤት ውስጥ የነበሩ አይሁድም፣ ብድግ ብላ መውጣቷን ሲያዩ፣ ወደ መቃብሩ ሄዳ የምታለቅስ መስሏቸው ተከተሏት። ማርያምም ኢየሱስ ወደ ነበረበት ቦታ ደርሳ እንዳየችው፣ እግሩ ላይ ተደፍታ፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ፣ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” አለችው። ኢየሱስም እርሷ ስታለቅስ፣ ተከትለዋትም የመጡት አይሁድም ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ መንፈሱ በሐዘን ታውኮ፣ “የት ነው ያኖራችሁት?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም፣ “ጌታ ሆይ፤ መጥተህ እይ” አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። አይሁድም፣ “እንዴት ይወድደው እንደ ነበር አያችሁ!” አሉ። ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን፣ “የዐይነ ስውሩን ዐይን የከፈተ፣ ይህም ሰው እንዳይሞት ማድረግ አይችልም ነበር?” አሉ። ኢየሱስ ልቡ ዳግመኛ በሐዘን ተነክቶ ወደ መቃብሩ መጣ፤ መቃብሩም በድንጋይ የተገጠመ ዋሻ ነበር፤ እርሱም፣ “ድንጋዩን አንሡት” አለ። የሟቹም እኅት ማርታ፣ “ጌታ ሆይ፤ አሁንማ አራት ቀን ስለ ቈየ ይሸታል” አለችው። ኢየሱስም፣ “ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርሁሽም?” አላት። ስለዚህ ድንጋዩን አነሡ። ኢየሱስም ወደ ላይ ተመልክቶ አንዲህ አለ፤ “አባት ሆይ፤ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ፤ ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ ዐውቃለሁ፤ ይህን መናገሬ ግን በዚህ የቆሙ ሰዎች አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ ነው።” ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ በታላቅ ድምፅ፣ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” ብሎ ተጣራ። የሞተውም ሰው እጅና እግሩ በቀጭን ስስ ጨርቅ እንደ ተጠቀለለ፣ ፊቱም በሻሽ እንደ ተጠመጠመ ወጣ። ኢየሱስም “መግነዙን ፍቱለትና ይሂድ” አላቸው። ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፣ ኢየሱስ ያደረገውን ካዩት አይሁድ ብዙዎች በርሱ አመኑ። አንዳንዶቹ ግን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ለፈሪሳውያን ተናገሩ፤ ከዚያም የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን የአይሁድን ሸንጎ ስብሰባ ጠሩ። እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው ብዙ ታምራዊ ምልክቶችን እያደረገ ስለ ሆነ ምን ብናደርግ ይሻላል? እንዲሁ ብንተወው ሰው ሁሉ በርሱ ያምናል፤ ሮማውያንም መጥተው ስፍራችንንና ሕዝባችንን ይወስዱብናል።” ከመካከላቸውም አንዱ፣ በዚያ ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረው ቀያፋ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “እናንተ እኮ ምንም አታውቁም! ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ ስለ ሕዝቡ አንድ ሰው ቢሞት የሚሻል መሆኑን አታስተውሉም።” ይህን ያለው ከራሱ አልነበረም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት እንደ መሆኑ፣ ኢየሱስ ለአይሁድ ሕዝብ እንደሚሞት ትንቢት መናገሩ ነበር፤ ለዚያም ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች በአንድነት ለመሰብሰብ ነው። ከዚያ ቀን ጀምሮም፣ ሊገድሉት አሤሩ። ስለዚህ ኢየሱስ ከዚያ ወዲያ በአይሁድ መካከል በይፋ አልተመላለሰም፤ ነገር ግን በምድረ በዳ አጠገብ ወደምትገኝ ኤፍሬም ወደ ተባለች መንደር ገለል አለ፤ በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ሰነበተ። የአይሁድ ፋሲካ እንደ ተቃረበም፣ በዓሉ ከመድረሱ በፊት የመንጻት ሥርዐት ለማድረግ ብዙዎች ከአገር ቤት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። ኢየሱስንም ይፈልጉት ነበር፤ በቤተ መቅደስም ቆመው፣ “ምን ይመስላችኋል? ለበዓሉ አይመጣ ይሆን?” ተባባሉ። የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ግን ኢየሱስን ይይዙት ዘንድ የት እንዳለ የሚያውቅ ሰው እንዲጠቍም ትእዛዝ ሰጥተው ነበር።
ዮሐንስ 11 ያንብቡ
ያዳምጡ ዮሐንስ 11
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዮሐንስ 11:17-57
9 ቀናት
እያንዳንዳቸው እየሱስ ክርስቶስ የህያው የእግዛብሔር ልጅ መሆኑን መልካም የምስራች ዜናን ያበስሩ ነበር። ይህ አጭር ቪዲዮ የኢሱስ ክርስቶስ የእያንዳንዱን ቀን ቁልፍ ተአምራትን በምሳሌ ይገልፃል።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች