ዮሐንስ 1:31-51

ዮሐንስ 1:31-51 NASV

እኔ ራሴ አላወቅሁትም ነበር፤ በውሃ እያጠመቅሁ የመጣሁትም እርሱ በእስራኤል ዘንድ እንዲገለጥ ነው።” ከዚያም ዮሐንስ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጠ፤ “መንፈስ እንደ ርግብ ከሰማይ ወርዶ በርሱ ላይ ሲያርፍ አየሁ፤ በውሃ እንዳጠምቅ የላከኝም፣ ‘በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው፣ መንፈስ ሲወርድና በርሱ ላይ ሲያርፍ የምታየው እርሱ ነው’ ብሎ እስከ ነገረኝ ድረስ እኔም አላወቅሁትም ነበር፤ አይቻለሁ፣ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እመሰክራለሁ።” በማግስቱም፣ ዮሐንስ ከሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋራ እንደ ገና እዚያው ቦታ ነበር፤ ኢየሱስንም በዚያ ሲያልፍ አይቶ፣ “እነሆ፤ የእግዚአብሔር በግ!” አለ። ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ይህን ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት። ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉት አየና፣ “ምን ትፈልጋላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “ረቢ፣ የት ትኖራለህ?” አሉት፤ “ረቢ” ማለት መምህር ማለት ነው። እርሱም፣ “ኑና እዩ” አላቸው። ስለዚህ ሄደው የት እንደሚኖር አዩ፤ በዚያም ዕለት ዐብረውት ዋሉ፤ ከቀኑም ዐሥር ሰዓት ያህል ነበር። ዮሐንስ የተናገረውን ሰምተው፣ ኢየሱስን ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበር። እንድርያስ በመጀመሪያ ያደረገው ወንድሙን ስምዖንን ፈልጎ፣ “መሲሑን አገኘነው” ብሎ መንገር ነው፤ “መሲሕ” ማለት ክርስቶስ ማለት ነው። ወደ ኢየሱስም አመጣው። ኢየሱስም ተመለከተውና፣ “አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ ኬፋ ተብለህ ትጠራለህ” አለው፤ “ኬፋ” ማለት ጴጥሮስ ማለት ነው። በማግስቱም፣ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ለመሄድ ፈለገ፤ ፊልጶስንም አግኝቶ፣ “ተከተለኝ” አለው። ፊልጶስም እንደ እንድርያስና እንደ ጴጥሮስ ሁሉ የቤተ ሳይዳ ከተማ ሰው ነበረ። ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ፣ “ሙሴ በሕግ መጻሕፍት፣ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስን አግኝተነዋል” አለው። ናትናኤልም፣ “ከናዝሬት በጎ ነገር ሊወጣ ይችላልን?” አለ። ፊልጶስም፣ “መጥተህ እይ” አለው። ኢየሱስም፣ ናትናኤል ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ፣ “እነሆ፤ ተንኰል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ” አለ። ናትናኤልም “እንዴት ዐወቅኸኝ?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “ከበለስ ዛፍ ሥር ሳለህ፣ ገና ፊልጶስ ሳይጠራህ አየሁህ” ሲል መለሰለት። ናትናኤልም መልሶ፣ “ረቢ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አለ። ኢየሱስም፣ “ያመንኸው ከበለስ ዛፍ ሥር አየሁህ ስላልሁህ ነውን? ገና ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ” አለው፤ ጨምሮም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማይ ተከፍቶ፣ የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ” አለው።