ሴዴቅያስ ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ አንድ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ዐሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ የእናቱም ስም አሚጣል ነበረ፣ እርሷም የልብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። ሴዴቅያስም ኢዮአቄም እንዳደረገው ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ። እንግዲህ ይህ ሁሉ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ሊደርስ የቻለው ከእግዚአብሔር ቍጣ የተነሣ ነበር፤ በመጨረሻም ከፊቱ አስወገዳቸው። በዚህ ጊዜ ሴዴቅያስ በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ። ስለዚህ ሴዴቅያስ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን፣ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሰራዊቱን ሁሉ አስከትቶ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ፤ ከተማዪቱንም ከበቧት፤ በዙሪያውም የዐፈር ድልድል ሠሩ። ከተማዪቱም እስከ ንጉሥ ሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት ዐሥራ አንደኛ ዓመት ድረስ እንዲሁ እንደ ተከበበች ቈየች። በአራተኛው ወር በዘጠነኛው ቀን በከተማዪቱ ራብ ጸንቶ ስለ ነበር ሕዝቡ የሚበላውን ዐጣ፤ የከተማዪቱም ቅጥር ተነደለ፤ ሰራዊቱም ሁሉ ኰብልሎ ሄደ። ባቢሎናውያን በከተማዪቱ ዙሪያ ቢኖሩም፣ በንጉሡ የአትክልት ስፍራ አጠገብ በሁለት ቅጥሮች መካከል ባለው በር በሌሊት ከተማዪቱን ጥለው ሸሹ፤ ወደ ዓረባም አመሩ። የባቢሎናውያንም ሰራዊት ንጉሥ ሴዴቅያስን ተከታትሎ በማሳደድ በኢያሪኮ ሜዳ ደረሱበት፤ ወታደሮቹም ሁሉ ከርሱ ተለይተው ተበታትነው ሳለ፣ ንጉሡን ያዙት። በዚያ ጊዜ በሐማት ምድር በሪብላ ወደ ነበረው ወደ ባቢሎንም ንጉሥ አመጡት፤ በዚያም የባቢሎን ንጉሥ ፈረደበት። በሪብላም የባቢሎን ንጉሥ፣ የሴዴቅያስን ወንዶች ልጆች በአባታቸው ፊት ገደላቸው፤ የይሁዳንም ባለሥልጣኖች ሁሉ ገደላቸው፤ የሴዴቅያስንም ዐይኖች አወጣ፤ በናስ ሰንሰለትም አሰረው። የባቢሎንም ንጉሥ ወደ ባቢሎን ወሰደው፤ በዚያም እስከ ዕለተ ሞቱ በእስር ቤት አቈየው። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በነገሠ በዐሥራ ዘጠነኛው ዓመት በዐምስተኛው ወር፤ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን፣ የባቢሎን ንጉሥ ባለሟል የክብር ዘበኞች አዛዥ የነበረው ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ፣ ቤተ መንግሥቱን እንዲሁም በኢየሩሳሌም የሚገኙትን ቤቶች ሁሉ በእሳት አቃጠለ፤ እያንዳንዱንም ትልልቅ ሕንጻዎችንም በእሳት አወደመ። በክብር ዘበኞቹ አዛዥ ሥር የነበሩት የባቢሎናውያን ሰራዊት ሁሉ በኢየሩሳሌም ዙሪያ ያለውን ቅጥር በሙሉ አፈረሱ። የክብር ዘቡ አዛዥ ናቡዘረዳን አንዳንድ የድኻ ድኾችንና በከተማዪቱ የቀረውን ሕዝብና ሸሽተው ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን ሰዎች ከእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ጋራ አፈለሳቸው። ሆኖም የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ናቡዘረዳን ሌሎች የምድሪቱን ድኾች፣ ወይን ተካዮችና ዐራሾች እንዲሆኑ አስቀራቸው። ባቢሎናውያን በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የነበሩትን የናስ ዐምዶች፣ ተንቀሳቃሽ የዕቃ ማስቀመጫዎችንና ከናስ የተሠራውን የውሃ ማጠራቀሚያ ሰባበሩ፤ ናሱንም ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰዱ። ከእነዚህም ሌላ ምንቸቶቹን፣ መጫሪያዎቹን፣ መኰስተሪያዎቹን፣ ወጭቶቹን፣ ጭልፋዎቹንና ለቤተ መቅደስ አገልግሎት የሚውሉትን የናስ ዕቃዎች በሙሉ ወሰዱ። የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ከንጹሕ ወርቅና ብር የተሠሩትን ዕቃዎች ሁሉ ጐድጓዳ ሳሕኖችን ጥናዎችን፣ ወጭቶችን፣ ምንቸቶችን፣ መቅረዞችን፣ ጭልፋዎችንና ለመጠጥ ቍርባን ማቅረቢያ የሚሆኑ ወጭቶችን ይዞ ሄደ። ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከናስ ያሠራቸው፦ ሁለቱ ዐምዶች፣ ትልቁ የውሃ ገንዳ፣ ከሥሩ ያሉት ዐሥራ ሁለት ወይፈኖችና ተንቀሳቃሽ ማስቀመጫዎች ክብደታቸው ከሚዛን በላይ ነበር። እያንዳንዱም ዐምድ ከፍታው ዐሥራ ስምንት ክንድ ዙሪያ ክቡም ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፤ ውስጡ ክፍት ስለ ሆነ የእያንዳንዱ ከንፈር ውፍረት አራት ጣት ነበረ። በአንዱ ዐምድ ዐናት ላይ ያለው የናስ ጕልላት ቁመት ዐምስት ክንድ ሲሆን፣ ዙሪያውንም ሁሉ የሮማን ቅርጽ ባላቸው የናስ ጌጣጌጦች የተዋበ ነበር፤ ሌላውም ዐምድ የሮማኑን ጌጣጌጥ ጨምሮ ከዚሁ ጋራ ተመሳሳይ ነበር። ዘጠና ስድስቱ ሮማኖች ከጐን በቀላሉ የሚታዩ ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ በዙሪያው ካለው ጌጥ በላይ ያለው የሮማኖች ቍጥር አንድ መቶ ነበር። የክብር ዘበኞቹ አዛዥም ሊቀ ካህኑን ሠራያን፣ በማዕርግ ከርሱ ቀጥሎ ያለውን ካህኑን ሶፎንያስንና ሦስቱን የበር ጠባቂዎች አስሮ ወሰዳቸው፤ በከተማው ውስጥ ከቀሩትም ሕዝብ፣ የተዋጊዎቹ ኀላፊ የነበረውን መኰንን፣ ሰባቱን የንጉሡን አማካሪዎች ከአገሬው ሕዝብ ወታደር የሚመለምለውን መኰንን ጸሓፊና በከተማው ውስጥ የተገኙትን ሌሎች ስድሳ ሰዎች ወሰደ። የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ናቡዘረዳን እነዚህን ሁሉ ይዞ የባቢሎን ንጉሥ ወደ ነበረበት ወደ ሪብላ አመጣቸው። ንጉሡም ሰዎቹን በሐማት ምድር በነበረችው በሪብላ ውስጥ አስገደላቸው። ይሁዳም ከምድሩ በዚህ ሁኔታ ተማርኮ ሄደ። ናቡከደነፆር ማርኮ የወሰደው ሕዝብ ቍጥር እንደሚከተለው ነው፦ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፣ ሦስት ሺሕ ሃያ ሦስት አይሁድ፤ ናቡከደነፆር በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት፣ ስምንት መቶ ሠላሳ ሁለት ሰዎች ከኢየሩሳሌም፤ ናቡከደነፆር በነገሠ በሃያ ሦስተኛው ዓመት፣ የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡዘረዳን፣ ሰባት መቶ አርባ ዐምስት አይሁድ ማርኮ ወስዷል። በአጠቃላይ አራት ሺሕ ስድስት መቶ ሰዎች ነበሩ። የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በተማረከ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት፣ ዮርማሮዴክ በባቢሎን ነገሠ፤ በዚሁ ዓመት፣ በዐሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በሃያ ዐምስተኛው ቀን የይሁዳን ንጉሥ ዮአኪንን ዐሰበው፤ ከእስር ቤትም አወጣው፤ በመልካምም ቃል አናገረው፤ ከርሱም ጋራ በባቢሎን በምርኮ ከነበሩት ነገሥታት ይልቅ ከፍ ባለ የክብር ቦታ አስቀመጠው። ዮአኪንም የእስር ቤት ልብሱን ጣለ፤ እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ ከንጉሡ ማእድ ዘወትር ይመገብ ነበር። የባቢሎንም ንጉሥ፣ ዮአኪን እስኪሞት ድረስ፣ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሳያቋርጥ በየዕለቱ ቀለቡን ይሰጠው ነበር።
ኤርምያስ 52 ያንብቡ
ያዳምጡ ኤርምያስ 52
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኤርምያስ 52:1-34
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች