ስለ ሕዝቦች ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤ ስለ ግብጽ፤ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት በአራተኛው ዓመት በኤፍራጥስ ወንዝ በከርከሚሽ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ባሸነፈው በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ኒካዑ ሰራዊት ላይ የተነገረ መልእክት ይህ ነው፤ “ትልቁንና ትንሹን ጋሻ አዘጋጁ፤ ለውጊያም ውጡ! ፈረሶችን ጫኑ፤ በላያቸውም ተቀመጡ! የራስ ቍር ደፍታችሁ፣ በየቦታችሁ ቁሙ፤ ጦራችሁን ወልውሉ፤ ጥሩራችሁን ልበሱ! ነገር ግን ይህ የማየው ምንድን ነው? እጅግ ፈርተዋል፤ ወደ ኋላ እያፈገፈጉ ነው፤ ብርቱ ጦረኞቻቸው ተሸንፈዋል፤ ዘወር ብለውም ሳያዩ፣ በፍጥነት እየሸሹ ነው፤ በየቦታውም ሽብር አለ፣” ይላል እግዚአብሔር። “ፈጣኑ መሸሽ አይችልም፤ ብርቱውም አያመልጥም፤ በሰሜን በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ፣ ተሰናክለው ወደቁ። “ይህ እንደ አባይ ወንዝ ሙላት የሚዘልለው፣ እንደ ደራሽ ወንዝ የሚፈስሰው ማነው? ግብጽ እንደ አባይ ወንዝ ሙላት ይዘልላል፤ እንደ ደራሽ ወንዝ ይወረወራል፤ ‘እወጣለሁ፤ ምድርንም እሸፍናለሁ፤ ከተሞችንና ነዋሪዎቻቸውን አጠፋለሁ’ ይላል። ፈረሶች ሆይ ዘልላችሁ ውጡ፤ ሠረገሎችም ሸምጥጡ፤ ጋሻ ያነገባችሁ የኢትዮጵያና የፉጥ ሰዎች፣ ቀስት የገተራችሁ የሉድ ጀግኖች፣ እናንተ ብርቱ ጦረኞች ተነሥታችሁ ዝመቱ። ያ ቀን ግን የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቀን ነው፤ ጠላቶቹን የሚበቀልበት የበቀል ቀን። ሰይፍ እስኪጠግብ ድረስ ይበላል፤ ጥማቱም እስኪረካ ድረስ ደም ይጠጣል። በሰሜን ምድር በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር መሥዋዕት አዘጋጅቷልና። “ድንግሊቱ የግብጽ ሴት ልጅ ሆይ፤ ወደ ገለዓድ ውጪ፤ የሚቀባ መድኀኒትም አምጪ፤ ነገር ግን መድኀኒት የምታበዢው በከንቱ ነው፤ ፈውስ አታገኚም። ሕዝቦች ኀፍረትሽን ይሰማሉ፤ ልቅሶሽም ምድርን ይሞላል። ጦረኛ በጦረኛው ይደናቀፋል፤ ሁለቱም ተያይዘው ይወድቃሉ።” የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር መጥቶ ግብጽን እንደሚወጋ፣ እግዚአብሔር ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረው መልእክት ይህ ነው፤ “ይህን በግብጽ ተናገር፤ በሚግዶልም አሰማ፤ በሜምፊስና በጣፍናስም እንዲህ ብለህ ዐውጅ፤ ‘በቦታችሁ ቁሙ፤ ተዘጋጁም፤ በዙሪያችሁ ያሉትን ሰይፍ ይበላቸዋልና።’ ጦረኞችህ ለምን ተዘረሩ? እግዚአብሔር ገፍትሮ ስለሚጥላቸው መቆም አይችሉም። ደጋግመው ይሰናከላሉ፣ አንዱም በሌላው ላይ ይወድቃል፤ ‘ተነሡ እንሂድ፤ ወደ ሕዝባችንና ወደ ትውልድ አገራችን እንመለስ፤ ከጠላትም ሰይፍ እናምልጥ’ ይላሉ። በዚያም የግብጽን ንጉሥ ፈርዖንን፣ ‘በተሰጠው ዕድል ያልተጠቀመ፣ አለሁ አለሁ ባይ ደንፊ!’ ብለው ይጠሩታል።” ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነው ንጉሡ እንዲህ ይላል፤ “በሕያውነቴ እምላለሁ”። በተራሮች መካከል ያለውን የታቦር ተራራ የሚመስል፣ ባሕርም አጠገብ ያለውን የቀርሜሎስ ተራራ የሚመስል አንድ የሚመጣ አለ። እናንተ በግብጽ የምትኖሩ ሆይ፤ በምርኮ ለመወሰድ ጓዛችሁን አሰናዱ፤ ሜምፊስ ፈራርሳ፣ ሰው የማይኖርባት ባድማ ትሆናለችና። “ግብጽ ያማረች ጊደር ናት፤ ነገር ግን ተናዳፊ ዝንብ ከሰሜን ይመጣባታል። ቅጥረኞች ወታደሮቿም እንደ ሠቡ ወይፈኖች ናቸው፤ የሚቀጡበት ጊዜ ስለ ደረሰ፣ ጥፋታቸው ስለ ተቃረበ፣ እነርሱም ወደ ኋላ ተመልሰው በአንድነት ይሸሻሉ፤ በቦታቸውም ጸንተው ሊቋቋሙ አይችሉም። ጠላት ገፍቶ ሲመጣባት፣ ግብጽ እንደሚሸሽ እባብ ታፏጫለች፤ ዛፍ እንደሚቈርጡ ሰዎች፣ መጥረቢያ ይዘው ይመጡባታል። ጥቅጥቅ ጫካ ቢሆንም፣ ደኗን ይመነጥራሉ፤” ይላል እግዚአብሔር፤ “ብዛታቸው እንደ አንበጣ ነው፤ ሊቈጠሩም አይችሉም። የግብጽ ሴት ልጅ ለኀፍረት ትጋለጣለች፤ ለሰሜን ሕዝብም ዐልፋ ትሰጣለች።” የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በቴብስ አምላክ በአሞን ላይ፣ በፈርዖን ላይ፣ በግብጽና በአማልክቷ ላይ፣ በነገሥታቷም ላይ፣ እንዲሁም በፈርዖን በሚታመኑት ላይ ቅጣት አመጣለሁ፤ ነፍሳቸውን ለሚሹት ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆርና ለጦር መኰንኖቹ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ግብጽ እንደ ቀድሞው ዘመን የሰው መኖሪያ ትሆናለች” ይላል እግዚአብሔር። “አገልጋዬ ያዕቆብ ሆይ፤ አትፍራ፤ እስራኤል ሆይ፤ አትሸበር፤ አንተን ከሩቅ ስፍራ፣ ዘርህንም ተማርኮ ከሄደበት ምድር አድናለሁ። ያዕቆብም ተመልሶ በሰላምና በርጋታ ይቀመጣል፤ የሚያስፈራውም አይኖርም። አገልጋዬ ያዕቆብ ሆይ፤ አትፍራ፤ እኔ ከአንተ ጋራ ነኝና” ይላል እግዚአብሔር፤ “አንተን የበተንሁበትን ሕዝብ ሁሉ፣ ፈጽሜ ባጠፋም እንኳ፣ አንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋህም። ተገቢውን ቅጣት እሰጥሃለሁ እንጂ፣ ያለ ቅጣት አልተውህም።”
ኤርምያስ 46 ያንብቡ
ያዳምጡ ኤርምያስ 46
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኤርምያስ 46:1-28
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች