በግብጽ ሰሜናዊ ክፍል በሚግዶል፣ በጣፍናስና በሜምፊስ እንዲሁም በግብጽ ደቡባዊ ክፍል ስለሚኖሩት የአይሁድ ሕዝብ እንዲህ የሚል ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ፤ “የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ላይ ያመጣሁትን ታላቅ ጥፋት አይታችኋል፤ ዛሬ ማንም የማይኖርባቸው ባድማ ሆነው ይታያሉ፤ ይህም የሆነው ስላደረጉት ክፋት ነው። እነርሱም ሆኑ እናንተ ወይም አባቶቻችሁ ላላወቋቸው ለሌሎች አማልክት በማጠንና በማምለክ አስቈጥተውኛል። እኔም፣ ‘ይህን የምጠላውን አስጸያፊ ነገር አታድርጉ’ በማለት አገልጋዮቼን ነቢያትን ደጋግሜ ላክሁባቸው። እነርሱ ግን አልሰሙም፤ ልብም አላሉም፤ ከክፋታቸው አልተመለሱም፤ ለሌሎችም አማልክት ማጠን አልተውም። ስለዚህ መዓቴና ቍጣዬ ፈሰሰ፤ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ላይ ነደደ፤ ዛሬ እንደሚታዩትም ማንም የማይኖርባቸው ፍርስራሾች አደረጋቸው። “አሁንም የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ዘር እንዳይቀርላችሁ ወንዶችና ሴቶች፣ ልጆችና ሕፃናት በይሁዳ እንዳይገኙ ለምን እንዲህ ዐይነት ታላቅ ጥፋት በራሳችሁ ላይ ታመጣላችሁ? ልትኖሩባት በመጣችሁባት በግብጽ ምድር ለሌሎች አማልክት በማጠን፣ እጆቻችሁ ባበጇቸው ነገሮች ለምን ታስቈጡኛላችሁ? በምድር ባሉት ሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የርግማንና የመዘባበቻ ምልክት ለመሆን ራሳችሁን ታጠፋላችሁን? በይሁዳ ምድርና በኢየሩሳሌም መንገዶች አባቶቻችሁ የይሁዳ ነገሥታትና ሚስቶቻቸው፣ እንዲሁም እናንተና ሚስቶቻችሁ ያደረጋችሁትን ክፋት ረስታችሁታልን? እስከ ዛሬ ድረስ ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ ክብርን አልሰጡኝም፤ በእናንተና በአባቶቻችሁ ፊት ያኖርሁትንም ሕጌንና ሥርዐቴን አልተከተሉም።’ “ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በእናንተ ላይ ጥፋት ለማምጣትና ይሁዳን ሁሉ ለመደምሰስ ቈርጬ ተነሥቻለሁ። ሄደው በግብጽ ለመቀመጥ የወሰኑትን የይሁዳ ቅሬታዎች ሁሉ እነጥቃለሁ፤ ሁሉም ይጠፋሉ፤ በግብጽ ምድር በሰይፍ ይወድቃሉ፤ በራብ ያልቃሉ፤ ከትንሽ እስከ ትልቅ በሰይፍና በራብ ይሞታሉ፤ የመነቀፊያና የድንጋጤ፣ የመረገሚያና የመዘባበቻ ምልክት ይሆናሉ። ኢየሩሳሌምን እንደ ቀጣሁ፣ በግብጽ የሚኖሩትን በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር እቀጣለሁ፤ ወደ ግብጽ የመጡት የይሁዳ ቅሬታዎች ወደ ይሁዳ ለመመለስ ቢመኙም ከጥቂት ስደተኞች በቀር አምልጦ ወይም ተርፎ ወደ ይሁዳ የሚመለስ አንድም ሰው አይኖርም።’ ” ሚስቶቻቸው ለሌሎች አማልክት ማጠናቸውን ያወቁ ወንዶች ሁሉና በዚያ የነበሩት ሴቶች ሁሉ ይህም ማለት በሰሜንና በደቡብ ግብጽ የሚኖረው ሕዝብ ሁሉ ታላቅ ጉባኤ ሆነው ለኤርምያስ እንዲህ አሉት፤ “አንተ በእግዚአብሔር ስም የነገርኸንን መልእክት አንሰማም፤ እናደርጋለን ያልነውን ሁሉ እናደርጋለን፤ አባቶቻችን፣ ነገሥታታችንና ባለሥልጣኖቻችን በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች እንዳደረጉት ሁሉ እኛም ለሰማይዋ ንግሥት እናጥናለን፤ የመጠጥ ቍርባን እናፈስስላታለን። በዚያ ጊዜ የተትረፈረፈ ምግብ ነበረን፤ በመልካም ሁኔታ እንገኝ ነበር እንጂ ምንም ክፉ ነገር አልገጠመንም። ነገር ግን ለሰማይዋ ንግሥት ማጠንና የመጠጥ ቍርባን ማፍሰስ ከተውን ወዲህ ሁሉን ነገር ዐጥተናል፤ በሰይፍና በራብም እያለቅን ነው።” ሴቶቹም፣ “ለሰማይዋ ንግሥት በምናጥንበትና የመጠጥ ቍርባን በምናፈስስበት ጊዜ፣ በምስሏ ዕንጐቻ ስንጋግርና የመጠጥ ቍርባን ስናፈስስላት ባሎቻችን አያውቁም ነበርን?” አሉ። ኤርምያስ ይህን መልስ ለሰጠው ሕዝብ፣ ለወንዶችና ለሴቶች ሁሉ እንዲህ አለ፤ “እናንተና አባቶቻችሁ፣ ነገሥታታችሁና ባለሥልጣኖቻችሁ እንዲሁም የምድሪቱ ሕዝብ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ያጠናችሁትን እግዚአብሔር የማያስታውሰውና የዘነጋው ይመስላችኋልን? እግዚአብሔር ክፉ አድራጎታችሁንና አስጸያፊ ተግባራችሁን ሊታገሥ ባለመቻሉ፣ ዛሬ እንደ ሆነው ምድራችሁ የርግማን ምልክትና ሰው የማይኖርበት ባዶ ምድረ በዳ ሆኗል። ዕጣን በማጠን በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአት ስለ ሠራችሁና ቃሉን ስላልጠበቃችሁ ሕጉን፣ ሥርዐቱንና ትእዛዙን ስላላከበራችሁ ዛሬ እንደምታዩት ጥፋት መጥቶባችኋል።” ኤርምያስም ለሕዝቡና ለሴቶቹ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “በግብጽ የምትኖሩ የይሁዳ ሕዝብ ሁሉ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እናንተና ሚስቶቻችሁ፣ “ለሰማይዋ ንግሥት ለማጠንና የመጠጥ ቍርባን ለማፍሰስ የተሳልነውን ስእለታችንን በርግጥ እንፈጽማለን” ብላችሁ የገባችሁትን ቃል በተግባር አሳይታችኋል።’ “እንግዲያውስ ወደ ኋላ አትበሉ፤ ቃል የገባችሁትን፣ ስእለታችሁንም ፈጽሙ። በግብጽ የምትኖሩ አይሁድ ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘ከእንግዲህ ወዲህ በየትኛውም የግብጽ ክፍል የሚኖር ማንኛውም አይሁዳዊ፣ “ሕያው እግዚአብሔርን!” ብሎ ስሜን እንዳይጠራ፣ እንዳይምልም በታላቁ ስሜ ምያለሁ፤ ለመልካም ሳይሆን ለክፉ እተጋባቸዋለሁና፤ በግብጽ የሚኖሩ አይሁድ ፈጽሞ እስኪጠፉ ድረስ በሰይፍና በራብ ይደመሰሳሉ። ከሰይፍ አምልጠው፣ ከግብጽ ወደ ይሁዳ ምድር የሚመለሱት በጣም ጥቂት ሰዎች ይሆናሉ። በግብጽ ምድር ለመኖር የመጡት የይሁዳ ቅሬታ ሁሉ፣ ከእኔ ወይም ከእነርሱ የማንኛችን ቃል እንደሚጸና ያውቃሉ። “ ‘በእናንተ ላይ አመጣለሁ ያልሁትን ክፉ ነገር እንደሚፈጸም ታውቁ ዘንድ በዚህ ስፍራ እንደምቀጣችሁ ይህ ምልክት ይሁናችሁ’ ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ ‘የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን ሊገድለው ለፈለገው ጠላቱ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር አሳልፌ እንደ ሰጠሁ፣ እንዲሁ የግብጽን ንጉሥ ፈርዖን ሖፍራን ሊገድሉት ለሚፈልጉ ጠላቶቹ አሳልፌ እሰጠዋለሁ።’ ”
ኤርምያስ 44 ያንብቡ
ያዳምጡ ኤርምያስ 44
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኤርምያስ 44:1-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች