ኤርምያስ 41:1-18

ኤርምያስ 41:1-18 NASV

ከንጉሣዊ ቤተ ሰብ የሆነው ከንጉሡ የጦር መኰንንኖች አንዱ የነበረው የኤሊሳማ ልጅ የናታንያ ልጅ እስማኤል፣ በሰባተኛው ወር ከዐሥር ሰዎች ጋራ ወደ ምጽጳ ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ መጣ፤ በዚያም በአንድነት ሊበሉ በማእድ ተቀምጠው ሳለ፣ የናታንያ ልጅ እስማኤልና ዐብረውት የነበሩ ዐሥሩ ሰዎች ተነሥተው፣ የባቢሎን ንጉሥ በምድሪቱ ላይ ገዥ አድርጎ የሾመውን የሳፋንን ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በሰይፍ መቱት፤ ገደሉትም። ደግሞም እስማኤል በምጽጳ ከጎዶልያስ ጋራ የነበሩትን አይሁድ ሁሉ፣ በዚያም የተገኙትን የባቢሎን ወታደሮች ገደላቸው። ጎዶልያስ በተገደለ ማግስት፣ ማንም ስለ ሁኔታው ከማወቁ በፊት፣ ሰማንያ ሰዎች ጢማቸውን ተላጭተው፣ ልብሳቸውን ቀድደው፣ ገላቸውን ነጭተው የእህል ቍርባንና ዕጣን በመያዝ ከሴኬም፣ ከሴሎና ከሰማርያ ወደ እግዚአብሔር ቤት ለማቅረብ መጡ። የናታንያ ልጅ እስማኤል ሊገናኛቸው እያለቀሰ ከምጽጳ ወጣ፤ ሲያገኛቸውም፣ “ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ኑ” አላቸው። ወደ ከተማዪቱ በገቡ ጊዜ፣ የናታንያ ልጅ እስማኤልና ዐብረውት የነበሩ ሰዎች ዐረዷቸው፤ በውሃ ማጠራቀሚያ ጕድጓድ ውስጥም ጣሏቸው። ከተገደሉት ጋራ የነበሩ ዐሥር ሰዎች ግን እስማኤልን፣ “እባክህ አትግደለን! በዕርሻችን ውስጥ የሸሸግነው ስንዴና ገብስ፣ የወይራ ዘይትና ማር ስላለን እባክህን አትግደለን” አሉት። እርሱም ተዋቸው፤ ከሌሎቹም ጋራ አልገደላቸውም። እስማኤል ከጎዶልያስ በተጨማሪ የገደላቸው ሰዎች ሁሉ ሬሳ የተጣለበት የውሃ ማጠራቀሚያ ጕድጓድ፣ ንጉሡ አሳ የእስራኤልን ንጉሥ ባኦስን ስለ ፈራ ለመከላከል ያሠራው ነበር፤ ይህን ጕድጓድ የናታንያ ልጅ እስማኤል በሬሳ ሞላው። እስማኤል በምጽጳ የቀረውን ሕዝብ ሁሉ ምርኮኛ አደረገ፤ እነርሱም የባቢሎን የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡዘረዳን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በላያቸው ገዥ አድርጎ የሾመባቸው የንጉሡ ሴቶች ልጆችና በዚያ የቀሩት ሌሎች ሰዎች ሁሉ ነበሩ። የናታንያ ልጅ እስማኤል እነዚህን ማርኮ ወደ አሞናውያን ለመሻገር ተነሣ። የቃሬያ ልጅ ዮሐናና ከርሱ ጋራ የነበሩት የጦር መኰንኖች ሁሉ የናታንያ ልጅ እስማኤል የፈጸመውን ግፍ ሁሉ በሰሙ ጊዜ፣ የናታንያን ልጅ እስማኤልን ሊወጉ ሰዎቻቸውን ሁሉ ይዘው ሄዱ፤ በገባዖንም ባለው በታላቁ ኵሬ አጠገብ ደረሱበት። እስማኤል የያዛቸው ሰዎች ሁሉ የቃሬያን ልጅ ዮሐናንንና ዐብረውት የነበሩትን የጦር መኰንኖች ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። እስማኤል ከምጽጳ ማርኮ የወሰዳቸው ሰዎች ሁሉ አምልጠው ወደ ቃሬያ ልጅ ወደ ዮሐናን ገቡ። የናታንያ ልጅ እስማኤል ግን ዐብረውት ከነበሩት ስምንት ሰዎች ጋራ ከዮሐናን አመለጠ፤ ሸሽቶም ወደ አሞናውያን ገባ። የቃሬያ ልጅ ዮሐናንና ከርሱ ጋራ የነበሩት የጦር መኰንኖች ሁሉ የናታንያ ልጅ እስማኤል የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን ከገደለ በኋላ፣ በምጽጳ ከማረካቸው የተረፉትን ሰዎች በማስመለስ ይዘው ሄዱ፤ እነዚህም፣ ወታደሮች፣ ሴቶች ሕፃናትና ከገባዖን ያመጧቸው የቤተ መንግሥት ባለሥልጣኖች ነበሩ። ከዚያም ተነሥተው ሄዱ፤ ወደ ግብጽም በማምራት በቤተ ልሔም አጠገብ ባለችው በጌሮት ከመዓም ዐረፉ፤ ወደ ግብጽም የሄዱት ከባቢሎናውያን ለማምለጥ ነበር፤ ባቢሎናውያንንም የፈሩት የናታንያ ልጅ እስማኤል የባቢሎን ንጉሥ የምድሪቱ ገዥ አድርጎ የሾመውን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በመግደሉ ነው።