ኤርምያስ ለሕዝቡ የተናገረውን ቃል የማታን ልጅ ሰፋጥያስ፣ የጳስኮር ልጅ ጎዶልያስ፣ የሰሌምያ ልጅ ዮካል እንዲሁም የመልክያ ልጅ ጳስኮር ሰሙ፤ ቃሉም እንዲህ የሚል ነበር፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በዚህች ከተማ የሚቀር ሁሉ በሰይፍ፣ በራብ ወይም በቸነፈር ይሞታል፤ ይህን ስፍራ ለቅቆ ወደ ባቢሎናውያን የሚሄድ ሁሉ ይተርፋል፤ ያመልጣል፤ በሕይወትም ይኖራል።’ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፤ ‘ይህች ከተማ በርግጥ ለባቢሎን ንጉሥ ሰራዊት ዐልፋ ትሰጣለች፤ እርሱም ይይዛታል።’ ” መኳንንቱም ንጉሡን እንዲህ አሉት፤ “ይህ ሰው በሚናገረው ነገር በዚህች ከተማ የቀሩትን ወታደሮችና ሕዝቡንም ሁሉ ተስፋ የሚያስቈርጥ ስለ ሆነ መሞት አለበት፤ ይህ ሰው የሕዝቡን መጥፋት እንጂ መልካም ነገር አይሻም።” ንጉሡ ሴዴቅያስም፤ “እርሱ በእጃችሁ ነው፤ ንጉሡ እናንተን ተቃውሞ ምንም ማድረግ አይችልም” አለ። ስለዚህ ኤርምያስን ወስደው፣ በዘበኞች አደባባይ በነበረው በንጉሡ ልጅ በመልክያ የውሃ ማጠራቀሚያ ጕድጓድ ውስጥ ጣሉት፤ በገመድም ኤርምያስን ወደ ጕድጓዱ አወረዱት። ጕድጓዱም ጭቃ እንጂ ውሃ አልነበረበትም፤ ኤርምያስም ወደ ጭቃው ዘልቆ ገባ። በቤተ መንግሥት ባለሥልጣን የነበረው ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ አቢሜሌክ፣ ኤርምያስን በውሃ ማጠራቀሚያ ጕድጓድ ውስጥ እንደ ጣሉት ሰማ። ንጉሡም በብንያም በር ተቀምጦ ሳለ፣ አቢሜሌክ ከቤተ መንግሥት ወጥቶ ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ እነዚህ ሰዎች በነቢዩ በኤርምያስ ላይ ባደረጉት ነገር ሁሉ ክፋትን አድርገዋል፤ ከከተማዪቱም እንጀራ በጠፋ ጊዜ በራብ እንዲሞት ጕድጓድ ውስጥ ጥለውታል።” ንጉሡም ኢትዮጵያዊውን አቢሜሌክን፣ “ሠላሳ ሰዎች ከዚህ ይዘህ ሂድ፤ ነቢዩ ኤርምያስንም ሳይሞት ከጕድጓድ አውጣው” ብሎ አዘዘው። አቢሜሌክም ሰዎቹን ይዞ በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ሥር ወዳለው ክፍል ሄደ፤ ያረጀ ጨርቅና ያለቀ ልብስ ከዚያ ወስዶ ወደ ኤርምያስ ወደ ጕድጓዱ ውስጥ በገመድ አወረደለት። ኢትዮጵያዊው አቢሜሌክ ኤርምያስን፣ “ይህን ያረጀ ጨርቅና ያረጀ ልብስ ገመዱ እንዳይከረክርህ በብብትህ ሥር አድርገው” አለው፤ ኤርምያስም እንዲሁ አደረገ፤ እነርሱም በገመዱ ጐትተው ከጕድጓዱ አወጡት። ኤርምያስም በዘበኞች አደባባይ ሰነበተ። ንጉሡ ሴዴቅያስ ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ ልኮ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሦስተኛው በር አስመጣውና፤ “አንድ ነገር እጠይቅሃለሁ፤ ምንም አትሸሽገኝ” አለው። ኤርምያስም ሴዴቅያስን፣ “መልስ ብሰጥህ አትገድለኝምን? ምክር ብሰጥህ አትሰማኝም” አለው። ንጉሥ ሴዴቅያስ፣ “ለኤርምያስ፣ እስትንፋስ የሰጠ ሕያው እግዚአብሔርን! በርግጥ አልገድልህም፤ ሕይወትህንም ለሚሿት አሳልፌ አልሰጥም” ብሎ በምስጢር ማለለት። ኤርምያስም ሴዴቅያስን እንዲህ አለው፤ “የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ለባቢሎን ንጉሥ የጦር መኰንኖች እጅህን ብትሰጥ፣ ሕይወትህ ትተርፋለች፤ ይህችም ከተማ አትቃጠልም፤ አንተና ቤተ ሰብህም በሕይወት ትኖራላችሁ። ለባቢሎን ንጉሥ የጦር መኰንኖች እጅህን ባትሰጥ ግን ይህች ከተማ ለባቢሎናውያን ዐልፋ ትሰጣለች፤ እነርሱም ያቃጥሏታል፤ አንተም ራስህ ከእጃቸው አታመልጥም።’ ” ንጉሡም ሴዴቅያስ ኤርምያስን፣ “ወደ ባቢሎን የኰበለሉት አይሁድ እንዲያላግጡብኝ፣ ባቢሎናውያን ለእነርሱ አሳልፈው ይሰጡኛል ብዬ እፈራለሁ” አለው። ኤርምያስም እንዲህ አለው፤ “አሳልፈው አይሰጡህም፤ ብቻ የምነግርህን የእግዚአብሔር ቃል ታዘዝ፤ መልካም ይሆንልሃል፤ ሕይወትህም ትተርፋለች። እጅህን ለመስጠት እንቢ ብትል ግን፣ እግዚአብሔር የገለጠልኝ ነገር ይህ ነው፤ በይሁዳ ቤተ መንግሥት የቀሩ ሴቶች ሁሉ ወደ ባቢሎናውያን ባለሥልጣኖች ይወሰዳሉ፤ ሴቶቹም እንዲህ ይላሉ፤ “ ‘እነዚያ የተማመንህባቸው ወዳጆችህ፣ አሳሳቱህ፤ አሸነፉህ። እግርህ ጭቃ ውስጥ ተሰንቅሯል፤ ወዳጆችህ ጥለውህ ሄደዋል።’ “ሚስቶችህና ልጆችህ ሁሉ ተወስደው ለባቢሎናውያን ይሰጣሉ፤ አንተም ራስህ በባቢሎን ንጉሥ ትያዛለህ እንጂ ከእጃቸው አታመልጥም፤ ይህችም ከተማ በእሳት ትቃጠላለች።” ሴዴቅያስም ኤርምያስን እንዲህ አለው፤ “ስለዚህ ስለ ተነጋገርነው ነገር ማንም አይወቅ፤ አለዚያ ትሞታለህ። መኳንንቱ ከአንተ ጋራ እንደ ተነጋገርሁ ሰምተው ወደ አንተ ቢመጡና፣ ‘ንጉሡን ምን እንዳልኸው፣ ንጉሡም ምን እንዳለህ ንገረን፤ ሳትደብቅ ንገረን፤ አለዚያ እንገድልሃለን’ ቢሉህ፣ ‘በዚያ እንዳልሞት ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ ብዬ ንጉሡን ስለምን ነበር’ በላቸው።” መኳንንቱ ሁሉ ወደ ኤርምያስ መጥተው ጠየቁት፤ እርሱም ንጉሡ ያዘዘውን ቃል ሁሉ ነገራቸው፤ ከንጉሡ ጋራ የተነጋገሩትን ነገር የሰማ አንድም ሰው ስላልነበረ፣ ከዚህ በላይ አላነጋገሩትም። ኢየሩሳሌም እስከ ተያዘችበት ቀን ድረስ ኤርምያስ በዘበኞች አደባባይ ተቀመጠ።
ኤርምያስ 38 ያንብቡ
ያዳምጡ ኤርምያስ 38
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኤርምያስ 38:1-28
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች