ኤርምያስ 31:7-26

ኤርምያስ 31:7-26 NASV

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ያዕቆብ በደስታ ዘምሩ፤ ስለ ሕዝቦች አለቃ እልል በሉ፤ ምስጋናችሁን አሰሙ፤ ‘እግዚአብሔር ሆይ፤ የእስራኤልን ቅሬታ፣ ሕዝብህን አድን’ በሉ። እነሆ፤ ከሰሜን ምድር አመጣቸዋለሁ፤ ከምድርም ዳርቻ እሰበስባቸዋለሁ፤ በመካከላቸውም ዕውሮችና ዐንካሶች፣ ነፍሰ ጡርና በምጥ ላይ ያሉ ሴቶች ይገኛሉ፤ ታላቅም ሕዝብ ሆነው ይመለሳሉ። እያለቀሱ ይመጣሉ፤ እያጽናናሁ አመጣቸዋለሁ፤ እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፣ ኤፍሬም በኵር ልጄ ነውና፣ በውሃ ምንጭ ዳር፣ በማይሰናከሉበት ቀና መንገድ እመራቸዋለሁ። “ሕዝቦች ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ሩቅ ባሉ የባሕር ጠረፎችም፣ ‘እስራኤልን የበተነ እርሱ ይሰበስበዋል፤ መንጋውንም እንደ እረኛ ይጠብቃል’ ብላችሁ ዐውጁ። እግዚአብሔር ያዕቆብን ይዋጀዋልና፤ ከርሱም ከሚበረቱት እጅ ይታደገዋልና። መጥተውም በጽዮን ተራራ ላይ በደስታ ይዘምራሉ፤ በእግዚአብሔርም ልግስና፣ በእህሉ፣ በወይን ጭማቂውና በዘይቱ፣ በፍየልና በበግ ጠቦት፣ በወይፈንና በጊደር ደስ ይሰኛሉ፤ ውሃ እንደማይቋረጥባት የአትክልት ስፍራ ይሆናሉ፤ ከእንግዲህም አያዝኑም። ኰረዶች ይዘፍናሉ፤ ደስም ይላቸዋል፤ ጐረምሶችና ሽማግሌዎችም ይፈነጥዛሉ፤ ልቅሷቸውን ወደ ደስታ እለውጣለሁ፤ ከሐዘናቸውም አጽናናቸዋለሁ፤ ደስታንም እሰጣቸዋለሁ። ካህናቱን አትረፍርፌ እባርካለሁ፤ ሕዝቤም በልግስናዬ ይጠግባል፤” ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የልቅሶና የታላቅ ዋይታ ድምፅ ከራማ ተሰማ፤ ራሔል ስለ ልጆቿ አለቀሰች፣ መጽናናትም እንቢ አለች፤ ልጆቿ ዐልቀዋልና።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ድምፅሽን ከልቅሶ፣ ዐይኖችሽንም ከእንባ ከልክይ፤ ድካምሽ ያለ ዋጋ አይቀርምና፤” ይላል እግዚአብሔር። “ከጠላት ምድር ይመለሳሉ፤ ስለዚህ ወደ ፊት ተስፋ አለሽ” ይላል እግዚአብሔር። “ልጆችሽ ወደ ገዛ ምድራቸው ይመለሳሉ። “የኤፍሬምን የሲቃ እንጕርጕሮ በርግጥ ሰምቻለሁ፤ ‘እንዳልተገራ ወይፈን ቀጣኸኝ፤ እኔም ተቀጣሁ። አንተ እግዚአብሔር አምላኬ ነህና፣ መልሰኝ፤ እኔም እመለሳለሁ። ከአንተ ከራቅሁ በኋላ፣ ተመልሼ ተጸጸትሁ፤ ባስተዋልሁም ጊዜ፣ ጭኔን መታሁ፤ የወጣትነት ውርደቴን ተሸክሜአለሁና ዐፈርሁ፤ ቀለልሁም።’ ኤፍሬም የምወድደው፣ ደስም የምሰኝበት ልጄ አይደለምን? ብዙ ጊዜ ተቃውሜው ብናገርም፣ መልሼ ስለ እርሱ ዐስባለሁ፤ አንጀቴ ይላወሳል፤ በታላቅ ርኅራኄም እራራለታለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር። “የጐዳና ምልክት አቁሚ፤ መንገድ አመልካች ትከዪ፤ የምትሄጂበትን መንገድ፣ አውራ ጐዳናውን አስተውዪ፤ ድንግሊቱ እስራኤል ሆይ፤ ተመለሺ፤ ወደ ከተሞችሽም ግቢ። አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ፤ እስከ መቼ ትቅበዘበዣለሽ? እግዚአብሔር በምድር ላይ አዲስ ነገር ይፈጥራል፤ ሴት በወንድ ላይ ከበባ ታደርጋለች።” የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ምርኳቸውን በመለስሁላቸው ጊዜ፣ እነርሱ በይሁዳ ምድርና በከተሞቿ፣ ‘አንተ የጽድቅ ማደሪያ ቅዱስ ተራራ ሆይ፤ እግዚአብሔር ይባርክህ!’ የሚል አነጋገር እንደ ገና ይጠቀማሉ። ገበሬዎችና ዘላን ከብት አርቢዎች በይሁዳና በከተሞቿ በአንድነት ይኖራሉ። የዛለችውን ነፍስ ዐድሳለሁ፤ የደከመችውንም አበረታለሁ።” በዚህ ጊዜ ከእንቅልፌ ነቅቼ ዙሪያዬን ተመለከትሁ፤ እንቅልፌም ጣፋጭ ሆኖልኝ ነበር።