“ከእስራኤል ቤትና፣ ከይሁዳ ቤት ጋራ” ይላል እግዚአብሔር፣ “አዲስ ኪዳን የምገባበት፣ ጊዜ ይመጣል። ከግብጽ አወጣቸው ዘንድ፣ እጃቸውን ይዤ በመራኋቸው ጊዜ፣ ከአባቶቻቸው ጋራ እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤ የእነርሱ ባል ሆኜ ሳለሁ፣ ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋልና።” ይላል እግዚአብሔር። “ነገር ግን ከዚያ ጊዜ በኋላ፣ ከእስራኤል ቤት ጋራ የምገባው ኪዳን ይህ ነው” ይላል እግዚአብሔር፤ “ሕጌን በአእምሯቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ። እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። ከእንግዲህ ማንም ሰው ባልንጀራውን፣ ወይም ወንድሙን፣ ‘እግዚአብሔርን ዕወቅ’ ብሎ አያስተምርም፤ ከትንሹ ጀምሮ እስከ ትልቁ፣ ሁሉም እኔን ያውቁኛልና፤” ይላል እግዚአብሔር። “በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤ ኀጢአታቸውንም ከእንግዲህ አላስብም።” በቀን እንድታበራ፣ ፀሓይን የመደበ፣ በሌሊት እንዲያበሩ፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ያዘዛቸው፣ የሞገዱ ድምፅ እንዲተምም፣ ባሕሩን የሚያናውጥ፣ ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነ እንዲህ ይላል፤ “ይህ ሥርዐት በፊቴ ከተሻረ፣” ይላል እግዚአብሔር፤ “በዚያ ጊዜ የእስራኤልም ዘር በፊቴ፣ መንግሥት መሆኑ ለዘላለም ይቀራል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በላይ ያሉትን ሰማያትን መለካት፣ በታችም ያሉትን የምድር መሠረቶች መመርመር ከተቻለ፣ በዚያ ጊዜ የእስራኤልን ዘር ሁሉ፣ ስላደረጉት ነገር ሁሉ እጥላቸዋለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር። “እነሆ ከሐናንኤል ግንብ ጀምሮ እስከ ማእዘኑ በር ድረስ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ይህች ከተማ ለእግዚአብሔር የምትሠራበት ጊዜ ይመጣል፤ መለኪያ ገመዱም ከዚያ ጀምሮ በቀጥታ ወደ ጋሬብ ኰረብታ፣ ዐልፎም ወደ ጎዓ ይዘረጋል። ሬሳና ዐመድ የሚጣልበት ሸለቆ በሙሉ፣ በምሥራቅ በኩል የቄድሮንን ሸለቆ ይዞ እስከ ፈረስ በር የሚደርሰው ደልዳላ ቦታ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል፤ ከእንግዲህም ከተማዪቱ አትነቀልም፤ አትፈርስምም።”
ኤርምያስ 31 ያንብቡ
ያዳምጡ ኤርምያስ 31
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኤርምያስ 31:31-40
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች