ኤርምያስ 30:17-22

ኤርምያስ 30:17-22 NASV

አንተን ግን መልሼ ጤነኛ አደርግሃለሁ፤ ቍስልህንም እፈውሳለሁ፤’ ይላል እግዚአብሔር። ‘የተናቀች ማንም የማይፈልጋት ጽዮን’ ብለውሃልና። “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘እነሆ የያዕቆብን ድንኳን ምርኮ እመልሳለሁ፤ ለማደሪያውም እራራለሁ፤ ከተማዪቱ በፍርስራሿ ጕብታ ላይ ትሠራለች፤ ቤተ መንግሥቱም በቀድሞ ቦታው ይቆማል። ከእነርሱም የምስጋና መዝሙር፣ የእልልታ ድምፅ ይሰማል። እኔ አበዛቸዋለሁ፤ ቍጥራቸውም አይቀንስም፣ አከብራቸዋለሁ፤ የተናቁም አይሆኑም። ልጆቻቸው እንደ ቀድሞው ይሆናሉ፤ ማኅበረ ሰቡም በፊቴ የጸና ይሆናል፤ የሚጨቍኗቸውን ሁሉ እቀጣለሁ። መሪያቸው ከራሳቸው ወገን ይሆናል፤ ገዣቸውም ከመካከላቸው ይነሣል፤ ወደ እኔ አቀርበዋለሁ፤ እርሱም ይቀርበኛል፤ አለዚያማ ደፍሮ፣ ወደ እኔ የሚቀርብ ማን ነው?’ ይላል እግዚአብሔር። ‘ስለዚህ እናንተ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ።’ ”