ኤርምያስ 30:1-17

ኤርምያስ 30:1-17 NASV

ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የነገርሁህን ቃል ሁሉ በመጽሐፍ ጻፈው። እነሆ፣ ሕዝቤን እስራኤልንና ይሁዳን’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር የምመልስበት ጊዜ ተቃርቧል፤ እነርሱም ይወርሷታል’ ይላል እግዚአብሔር።” እግዚአብሔር ስለ እስራኤልና ስለ ይሁዳ የተናገረው ቃል ይህ ነው፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘የፍርሀትና የሽብር ጩኸት ተሰምቷል፤ ሰላምም የለም። እስኪ ጠይቁ፤ ተመልከቱም፤ ወንድ መውለድ ይችላል? ታዲያ ወንድ ሁሉ ምጥ እንደ ያዛት ሴት፣ እጁን በሆዱ ላይ አድርጎ፣ የሰውስ ሁሉ ፊት ጠቍሮ የማየው ለምንድን ነው? ወዮ ለዚያ ቀን! እንደዚያም ያለ አይኖርም፤ ለያዕቆብ የመከራ ጊዜ ነው፤ ነገር ግን ይተርፋል። “ ‘በዚያ ቀን’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ‘በጫንቃቸው ላይ ያለውን ቀንበር እሰብራለሁ፤ እስራታቸውንም እበጥሳለሁ፤ ከእንግዲህ ባዕዳን አይገዟቸውም። ነገር ግን ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር፣ ለማስነሣላቸውም ለንጉሣቸው፣ ለዳዊት ይገዛሉ። “ ‘ስለዚህ፤ አገልጋዬ ያዕቆብ ሆይ፤ አትፍራ፤ እስራኤል ሆይ፤ አትደንግጥ፤’ ይላል እግዚአብሔር። ‘አንተን ከሩቅ አገር፣ ዘርህንም ከተማረኩበት ምድር እታደጋለሁ፤ ያዕቆብ ተመልሶ በሰላምና በርጋታ ይቀመጣል፤ የሚያስፈራውም አይኖርም። እኔ ከአንተ ጋራ ነኝ፤ አድንሃለሁም’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘በአሕዛብ መካከል በትኜሃለሁ፤ እነዚህን አሕዛብ ሁሉ ፈጽሜ አጠፋለሁ፤ አንተን ግን ሙሉ በሙሉ አላጠፋህም፤ በመጠኑ እቀጣሃለሁ እንጂ፣ ያለ ቅጣት አልተውህም።’ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘ስብራትህ የማይጠገን፣ ቍስልህም የማይድን ነው። የሚሟገትልህ ሰው የለም፤ ለቍስልህ መድኀኒት አይኖርም፤ ፈውስም አታገኝም። ወዳጆችህ ሁሉ ረስተውሃል፤ ስለ አንተም ግድ የላቸውም። ጠላት እንደሚመታ መታሁህ፤ እንደ ጨካኝም ቀጣሁህ፤ በደልህ ታላቅ፣ ኀጢአትህም ብዙ ነውና። ፈውስ ለማይገኝለት ሕመምህ፣ ስለ ቍስልህ ለምን ትጮኻለህ? በደልህ ታላቅ፣ ኀጢአትህም ብዙ ስለ ሆነ፣ እነዚህን ሁሉ አድርጌብሃለሁና። “ ‘ነገር ግን አሟጥጠው የበሉህ ሁሉ እንደዚያው ይበላሉ፤ ጠላቶችህ ሁሉ ለምርኮ ዐልፈው ይሰጣሉ፤ የሚዘርፉህ ይዘረፋሉ፤ የሚበዘብዙህም ሁሉ ይበዘበዛሉ። አንተን ግን መልሼ ጤነኛ አደርግሃለሁ፤ ቍስልህንም እፈውሳለሁ፤’ ይላል እግዚአብሔር። ‘የተናቀች ማንም የማይፈልጋት ጽዮን’ ብለውሃልና።