ኤርምያስ 29:4-14

ኤርምያስ 29:4-14 NASV

የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ላስማረካቸው ሁሉ እንዲህ ይላል፤ “ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ፤ አትክልት ተክላችሁ ፍሬውን ብሉ፤ አግብታችሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ውለዱ፤ ወንዶች ልጆቻችሁንና ሴቶች ልጆቻችሁን አጋቡ፤ እነርሱም ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ይውለዱ፤ ቍጥራችሁም በዚያ ምድር ይብዛ እንጂ አይነስ። ተማርካችሁ ለሄዳችሁባት ከተማ ሰላምና ብልጽግናን እሹ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸልዩላት፤ ምክንያቱም እርሷ ብትበለጽግ እናንተም ትበለጽጋላችሁ።” የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በርግጥ እንዲህ ይላልና፤ “በመካከላችሁ ያሉት ነቢያትና ጠንቋዮች አያታልሏችሁ፤ የሚያልሙላችሁንም ሕልም አትስሙ፤ በስሜ ሐሰተኛ ትንቢት ይነግሯችኋል እንጂ እኔ አልላክኋቸውም” ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሰባው ዓመት የባቢሎን ቈይታችሁ በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ ልመልሳችሁ የገባሁላችሁን መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ። ለእናንተ ያለኝን ዕቅድ እኔ ዐውቃለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ዕቅዱም ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጣችሁ፣ የሰላም ሐሳብ እንጂ ለክፉ አይደለም። እናንተም ትጠሩኛላችሁ፤ ቀርባችሁ ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተ ትፈልጉኛላችሁ፤ በፍጹም ልባችሁም ከፈለጋችሁኝ ታገኙኛላችሁ፤ እኔም እገኝላችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ከምርኮም እመልሳችኋለሁ፤ እናንተንም ከበተንሁበት አገርና ስፍራ ሁሉ እመልሳችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “በምርኮ ምክንያት ወዳስለቀቅኋችሁም ምድር እመልሳችኋለሁ።”