ነቢዩ ኤርምያስ በምርኮ ተወስደው በሕይወት ለቀሩት ሽማግሌዎች፣ ለካህናቱ፣ ለነቢያቱና ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማርኮ ለወሰዳቸው ሕዝብ ሁሉ የላከው የደብዳቤ ቃል ይህ ነው፤ ይህም የሆነው ንጉሡ ኢኮንያን እቴጌዪቱ እናቱ፣ የቤተ መንግሥቱ ባለሟሎች፣ የይሁዳና የኢየሩሳሌም መሪዎች፣ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና ብረት ቀጥቃጮች ተማርከው ከኢየሩሳሌም ከተወሰዱ በኋላ ነበር። ደብዳቤውንም ከይሁዳ ንጉሥ ከሴዴቅያስ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር በተላኩት መልእክተኞች በሳፋን ልጅ በኤልዓሣና በኬልቅያስ ልጅ በገማርያ እጅ ላከው፤ ደብዳቤውም እንዲህ የሚል ነበር፤ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ላስማረካቸው ሁሉ እንዲህ ይላል፤ “ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ፤ አትክልት ተክላችሁ ፍሬውን ብሉ፤ አግብታችሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ውለዱ፤ ወንዶች ልጆቻችሁንና ሴቶች ልጆቻችሁን አጋቡ፤ እነርሱም ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ይውለዱ፤ ቍጥራችሁም በዚያ ምድር ይብዛ እንጂ አይነስ። ተማርካችሁ ለሄዳችሁባት ከተማ ሰላምና ብልጽግናን እሹ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸልዩላት፤ ምክንያቱም እርሷ ብትበለጽግ እናንተም ትበለጽጋላችሁ።” የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በርግጥ እንዲህ ይላልና፤ “በመካከላችሁ ያሉት ነቢያትና ጠንቋዮች አያታልሏችሁ፤ የሚያልሙላችሁንም ሕልም አትስሙ፤ በስሜ ሐሰተኛ ትንቢት ይነግሯችኋል እንጂ እኔ አልላክኋቸውም” ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሰባው ዓመት የባቢሎን ቈይታችሁ በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ ልመልሳችሁ የገባሁላችሁን መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ። ለእናንተ ያለኝን ዕቅድ እኔ ዐውቃለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ዕቅዱም ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጣችሁ፣ የሰላም ሐሳብ እንጂ ለክፉ አይደለም።
ኤርምያስ 29 ያንብቡ
ያዳምጡ ኤርምያስ 29
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኤርምያስ 29:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች