ኤርምያስ 23:1-9

ኤርምያስ 23:1-9 NASV

“በማሰማሪያ ቦታዬ ያሉትን በጎቼን ለሚያጠፉና ለሚበትኑ እረኞች ወዮላቸው!” ይላል እግዚአብሔር። ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሕዝቤን ስለሚጠብቁ እረኞች እንዲህ ይላል፤ “መንጋዬን ስለ በተናችሁ፣ ስላባረራችሁና ተገቢውን ጥንቃቄ ስላላደረጋችሁላቸው፣ ለክፋታችሁ ተገቢውን ቅጣት አመጣባችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “የመንጋዬንም ቅሬታ ካባረርሁባቸው አገሮች ሁሉ እኔ ራሴ ሰብስቤ፣ ወደ መሰማሪያቸው እመልሳቸዋለሁ፤ በዚያም ፍሬያማ ይሆናሉ፤ ይበዛሉም። የሚጠብቋቸውን እረኞች አስነሣላቸዋለሁ፤ ከእንግዲህም አይፈሩም፤ አይደነግጡም፤ ከእነርሱም አንድ እንኳ አይጐድልም” ይላል እግዚአብሔር። “እነሆ፤ ለዳዊት፣ ጻድቅ ቅርንጫፍ የማስነሣበት ጊዜ ይመጣል፤ እርሱም ፍትሕንና ጽድቅን የሚያደርግ፣ በጥበብ የሚገዛ ንጉሥ ይሆናል” ይላል እግዚአብሔር። በርሱም ዘመን ይሁዳ ይድናል፤ እስራኤልም ያለ ሥጋት ይኖራል፤ የሚጠራበትም ስም፣ “እግዚአብሔር ጽድቃችን” የሚል ይሆናል። “ስለዚህ ሰዎች፣ ‘እስራኤላውያንን ከግብጽ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን!’ ብለው ከእንግዲህ የማይምሉበት ዘመን ይመጣል ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን፣ ‘እስራኤልን ከሰሜን ምድርና እነርሱን ከበተነባቸው ከሌሎች አገሮች ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን’ ይላሉ፤ ከዚያ በኋላ በገዛ ምድራቸው ይኖራሉ።” ስለ ነቢያት፣ ልቤ በውስጤ ተሰብሯል፤ ዐጥንቶቼም ተብረክርከዋል፤ ከእግዚአብሔር የተነሣ፣ ከቅዱስ ቃሉም የተነሣ፣ የወይን ጠጅ እንዳሸነፈው፣ እንደ ሰካራም ሰው ሆኛለሁ።