እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “ሄደህ የይሁዳ ነገሥታት በሚገቡበትና በሚወጡበት በሕዝቡ በር በሌሎቹም የኢየሩሳሌም በሮች ሁሉ ቁም፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘በእነዚህ በሮች የምትገቡ የይሁዳ ነገሥታት ሆይ፤ የይሁዳ ሕዝብና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሁሉ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በሰንበት ቀን ሸክም ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች እንዳታስገቡ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። አባቶቻችሁን እንዳዘዝኋቸው ሰንበትን አክብሩ እንጂ በሰንበት ቀን ከየቤታችሁ ሸክም ይዛችሁ አትውጡ፤ ምንም ሥራ አትሥሩ።” እነርሱ ግን አልሰሙም፤ ልብም አላሉም፤ እንዳይሰሙና እንዳይገሠጹም ዐንገታቸውን አደነደኑ። ነገር ግን በጥንቃቄ ብትታዘዙኝ ይላል እግዚአብሔር፤ በሰንበትም ቀን በዚህች ከተማ በሮች ሸክም ይዛችሁ ባትገቡ፣ የሰንበትንም ቀን ምንም ሳትሠሩ ብትቀድሱት፣ በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታትና መኳንንታቸው በዚህች ከተማ በሮች ይገባሉ፤ በፈረሶችና በሠረገሎች ተቀምጠው በይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ታጅበው ይመጣሉ፤ ይህችም ከተማ ለዘላለም የሰው መኖሪያ ትሆናለች። ሰዎች ከይሁዳ ከተሞች፣ ከኢየሩሳሌም ዙሪያ፣ ከብንያምም አገር፣ ከቈላውና ከደጋው አገር እንዲሁም ከኔጌብ የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባን፣ ዕጣንና የምስጋና መሥዋዕት ይዘው ወደ እግዚአብሔር ቤት ይመጣሉ። ነገር ግን የሰንበትን ቀን ሳትቀድሱ፣ በሰንበት ቀን ሸክም ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች በመግባት ትእዛዜን ብትጥሱ፣ በኢየሩሳሌም በሮች ላይ ምሽጎቿን የሚበላ፣ የማይጠፋ እሳት እጭራለሁ።’ ”
ኤርምያስ 17 ያንብቡ
ያዳምጡ ኤርምያስ 17
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኤርምያስ 17:19-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች