ይሩባኣል የተባለው ጌዴዎን፣ ከርሱም ጋራ የነበሩት ሰዎች ሁሉ በጧት ተነሥተው በሐሮድ ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ። የምድያማውያንም ሰፈር እስራኤላውያን ከሰፈሩበት በስተሰሜን በኩል፣ በሞሬ ኰረብታ አጠገብ በሸለቆው ውስጥ ነበር። እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “ምድያማውያንን በእጃቸው አሳልፌ እንዳልሰጥ ዐብረውህ ያሉት ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው፤ እስራኤላውያን የገዛ ኀይላቸው እንዳዳናቸው በመቍጠር እንዳይታበዩብኝ፣ ‘ማንም የፈራ ቢኖር የገለዓድን ተራራ ትቶ ወደ መጣበት ይመለስ’ ብለህ ለሕዝቡ ዐውጅ።” ስለዚህ ሃያ ሁለቱ ሺሕ ሲመለሱ ዐሥሩ ሺሕ ብቻ ቀሩ። እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “አሁንም ሰዎቹ ብዙ ናቸው፤ ወደ ወንዝ ይዘሃቸው ውረድ፤ በዚያም እለይልሃለሁ። ‘ይህ ከአንተ ጋራ ይሂድ’ የምለው፣ ከአንተ ጋራ ይሄዳል፤ ነገር ግን፣ ‘ይህ ከአንተ ጋራ አይሂድ’ የምለው፣ ከአንተ ጋራ አይሄድም።” ስለዚህ ጌዴዎን ሰዎቹን ወደ ወንዝ ይዟቸው ወረደ፤ እዚያም እግዚአብሔር፣ “ውሻ በምላሱ እየጨለፈ እንደሚጠጣ ሁሉ፣ በምላሳቸው የሚጠጡትን፣ በጕልበታቸው ተንበርክከው ከሚጠጡት ለይ” አለው። ሦስት መቶ ሰዎች ውሃውን በእጃቸው እያፈሱ ጠጡ፤ የቀሩት ሁሉ ግን ለመጠጣት በጕልበታቸው ተንበረከኩ። እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፣ “ውሃውን በእጃቸው እያፈሱ በጠጡት ሦስት መቶ ሰዎች አድናችኋለሁ፤ ምድያማውያንንም በእጃችሁ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ የቀሩት በሙሉ ወደ የመጡበት ይመለሱ” አለው። ጌዴዎንም የቀሩትን እስራኤላውያን በሙሉ ወደየድንኳናቸው እንዲመለሱ አደረገ፤ ሦስት መቶውን ግን አስቀራቸው፤ እነርሱም የሚመለሱትን ሰዎች ስንቅና መለከት ወሰዱ። በዚህ ጊዜ የምድያማውያኑ ሰፈር ከእነርሱ በታች በሸለቋማው ውስጥ ነበር።
መሳፍንት 7 ያንብቡ
ያዳምጡ መሳፍንት 7
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መሳፍንት 7:1-8
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች