ያዕቆብ 3:7-17

ያዕቆብ 3:7-17 NASV

ማንኛውም ዐይነት እንስሳ፣ አዕዋፍ እንዲሁም በምድር ላይ የሚሳቡና፣ በባሕር ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታት ሁሉ መገራት ችለዋል፤ በሰውም ተገርተዋል። ነገር ግን ምላስን መግራት የሚችል ማንም ሰው የለም፤ የሚገድል መርዝ የሞላባትና ዕረፍት የሌላት ክፉ ነገር ናት። በምላሳችን ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በርሷም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን። ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣል። ወንድሞቼ ሆይ፤ ይህ ሊሆን አይገባም። ከአንድ ምንጭ ጣፋጭ ውሃና መራራ ውሃ ይመነጫልን? ወንድሞቼ ሆይ፤ በለስ ወይራን ወይንም በለስን ሊያፈራ ይችላልን? እንዲሁም ከጨው ውሃ ጣፋጭ ውሃ ሊገኝ አይችልም። ከእናንተ መካከል ጥበበኛና አስተዋይ የሆነ ሰው ማን ነው? ሥራውን ከጥበብ በሆነ በመልካም አኗኗር ያሳይ። ነገር ግን መራራ ቅናትና ራስ ወዳድነት በልባችሁ ቢኖር ኵራት አይሰማችሁ፤ እውነትንም አትካዱ። እንዲህ ያለችዋ ጥበብ ከላይ አይደለችም፤ ነገር ግን ከምድር፣ ከሥጋና ከአጋንንት ናት። ቅናትና ራስ ወዳድነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ ይገኛሉ። ከሰማይ የሆነችው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ በኋላም ሰላም ወዳድ፣ ታጋሽ፣ ዕሺ ባይ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬ የሞላባት፣ አድልዎና ግብዝነት የሌለባት ናት።