ኢሳይያስ 9:8-17

ኢሳይያስ 9:8-17 NASV

ጌታ በያዕቆብ ላይ ቃል ላከ፤ በእስራኤልም ላይ ይወድቃል። ሕዝቡ በሙሉ፣ ኤፍሬምና የሰማርያ ነዋሪዎች ይህን ያውቃሉ፤ በትዕቢትና በልብ እብሪትም እንዲህ ይላሉ፤ “ጡቦቹ ወድቀዋል፤ እኛ ግን በጥርብ ድንጋይ መልሰን እንገነባለን፤ የሾላ ዛፎቹ ተቈርጠዋል፤ እኛ ግን በዝግባ እንተካለን።” ነገር ግን እግዚአብሔር የረአሶንን ጠላቶች አጠንክሯል፤ በርሱም ላይ ባላጋራዎቹን ያነሣሣበታል። ሶርያውያን ከምሥራቅ፣ ፍልስጥኤማውያን ከምዕራብ፤ አፋቸውን ከፍተው እስራኤልን ይቦጫጭቋታል። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው ገና አልበረደም፤ እጁም እንደ ተነሣ ነው። ሕዝቡ ግን ወደ ቀጣቸው ፊታቸውን አልመለሱም፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርንም አልፈለጉም። ስለዚህ እግዚአብሔር ራስንና ጅራትን፣ የዘንባባውን ቅርንጫፍና ሸንበቆውን ከእስራኤል በአንድ ቀን ይቈርጣል። ሽማግሌዎችና የተከበሩ ሰዎች ራስ፣ ሐሰትን የሚያስተምሩ ነቢያት ደግሞ ጅራት ናቸው። ይህን ሕዝብ የሚመሩት ያስቱታል፤ የሚመራውም ሕዝብ ከመንገድ ወጥቶ ይባዝናል። ስለዚህ ጌታ በጐበዛዝት ደስ አይሰኝም፤ አባት ለሌላቸውና ለመበለቶች አይራራም፤ ሁሉም ፈሪሀ እግዚአብሔር ያላደረበትና ክፉ አድራጊ ነው፤ የሁሉ አፍ አስጸያፊ ቃል ይናገራልና።