ኢሳይያስ 9:1-6

ኢሳይያስ 9:1-6 NASV

ነገር ግን ተጨንቀው የነበሩ ከእንግዲህ ተስፋ ቢስ አይሆኑም። በቀደመው ዘመን የዛብሎንንና የንፍታሌምን ምድር አዋረደ፤ በሚመጣው ዘመን ግን ከዮርዳኖስ ማዶ፣ በባሕር መንገድ አጠገብ ያለውን የአሕዛብን ገሊላ ያከብራል፤ በጨለማ የሚኖር ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ ምድር ላሉትም ብርሃን ወጣላቸው። ሕዝብን አበዛህ፤ ደስታቸውንም ጨመርህ፤ ሰዎች ምርትን ሲሰበስቡ፣ ምርኮንም ሲከፋፈሉ ደስ እንደሚላቸው ሁሉ፣ እነርሱም በፊትህ ደስ ይላቸዋል። ምድያም ድል በተመታ ጊዜ እንደ ሆነው፣ የከበዳቸውን ቀንበር፣ በትከሻቸው ላይ የነበረውን በትር፣ የተጨቈኑበትንም ዘንግ ሰብረህላቸዋል። የጦረኞች ጫማ ሁሉ፣ በደም የተለወሰ ልብስም ሁሉ፣ ለእሳት ይዳረጋል፤ ይማገዳልም። ሕፃን ተወልዶልናል፤ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል። ስሙም፣ ድንቅ መካር፣ ኀያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም ልዑል ይባላል።