እንደ ገናም እግዚአብሔር አካዝን እንዲህ አለው፤ “ከጥልቁ ጥልቅ ወይም ከከፍታው ከፍታ ምልክት እንዲሰጥህ ከእግዚአብሔር ከአምላክህ ለምን።” አካዝ ግን፣ “አልለምንም፣ እግዚአብሔርንም አልፈታተንም” አለ። ኢሳይያስም እንዲህ አለ፤ “እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፤ ስሙ! የሰውን ትዕግሥት መፈታተናችሁ አንሶ የአምላኬን ትዕግሥት ትፈታተናላችሁን? ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም ዐማኑኤል ትለዋለች። ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ሲችል ቅቤና ማር ይበላል። ነገር ግን ሕፃኑ ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ከመቻሉ በፊት የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት ምድር ባድማ ይሆናል። ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ዘመን በአንተ፣ በሕዝብህና በአባትህ ቤት ላይ ያመጣል፤ የሚያመጣውም የአሦርን ንጉሥ ነው።” በዚያ ቀን እግዚአብሔር ራቅ ካሉት ከግብጽ ወንዞች ዝንቦችን፣ ከአሦርም ምድር ንቦችን በፉጨት ይጠራል። እነርሱም በሙሉ መጥተው፣ በየበረሓው ሸለቆ፣ በየዐለቱ ንቃቃት፣ በየእሾኹ ቍጥቋጦና በየውሃው ጕድጓድ ሁሉ ይሰፍራሉ። በዚያ ቀን፣ እግዚአብሔር ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ በተከራየው ምላጭ፣ ማለትም በአሦር ንጉሥ፣ የራስና የእግር ጠጕራችሁን እንዲሁም ጢማችሁን ይላጫል። በዚያ ቀን፣ አንድ ሰው አንዲት ጊደርና ሁለት በግ ብቻ ይተርፈዋል። ከሚሰጡትም የተትረፈረፈ ወተት ቅቤ ይበላል፤ በምድሪቱም የቀሩ ሁሉ ቅቤና ማር ይበላሉ። በዚያ ቀን ሺሕ ሰቅል ብር የሚያወጣ አንድ ሺሕ የወይን ተክል የነበረበት ቦታ ሁሉ፣ ኵርንችትና እሾኽ ብቻ ይሆናል። ምድሪቱ በኵርንችትና በእሾኽ ስለምትሸፈን፣ ሰዎች ወደዚያ የሚገቡት ቀስትና ፍላጻ ይዘው ነው፤ ኵርንችትና እሾኹን በመፍራት ከዚህ በፊት በመቈፈሪያ ተቈፍረው ወደ ነበሩት ወደ እነዚያ ኰረብቶች ሁሉ ከእንግዲህ አትሄድም፤ ነገር ግን የከብቶች መሰማሪያና የበጎች መፈንጫ ቦታ ይሆናሉ።
ኢሳይያስ 7 ያንብቡ
ያዳምጡ ኢሳይያስ 7
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኢሳይያስ 7:10-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች