ኢሳይያስ 64:2-7

ኢሳይያስ 64:2-7 NASV

እሳት ሲለኰስ ጭራሮን እንደሚያቀጣጥል፣ ውሃንም እንደሚያፈላ፣ ስምህ በጠላቶችህ ዘንድ እንዲታወቅ ውረድ፤ መንግሥታትም በፊትህ እንዲንቀጠቀጡ አድርግ! እኛ ያልጠበቅነውን አስፈሪ ነገር ባደረግህ ጊዜ፣ አንተ ወረድህ፤ ተራሮችም በፊትህ ተንቀጠቀጡ። ከጥንት ጀምሮ፣ በተስፋ ለሚጠባበቁት የሚደርስላቸው፣ ከአንተ በቀር አምላክ እንዳለ ያየ ዐይን የለም፤ የሰማም ጆሮ የለም። በደስታ ቅን ነገር የሚያደርጉትን፣ መንገድህን የሚያስቡትንም ትረዳለህ፤ እኛ ግን በእነርሱ ላይ ሳናቋርጥ ኀጢአት በመሥራታችን፣ እነሆ፤ ተቈጣህ፤ ታዲያ እንዴት መዳን እንችላለን? ሁላችን እንደ ረከሰ ሰው ሆነናል፤ የጽድቅ ሥራችን እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችን እንደ ቅጠል ረግፈናል፤ ኀጢአታችንም እንደ ነፋስ ጠራርጎናል። ማንም በጸሎት ስምህን አይጠራም፤ አንተንም ለመያዝ የሚሞክር የለም፤ ፊትህን ከእኛ ሰውረሃል፤ ስለ ኀጢአታችንም ትተኸናል።