“ብርሃንሽ መጥቷልና ተነሺ አብሪ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻል። እነሆ፤ ጨለማ ምድርን፣ ድቅድቅ ጨለማም ሕዝቦችን ይሸፍናል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ወጥቶልሻል፤ ክብሩንም ይገልጥልሻል። ሕዝቦች ወደ ብርሃንሽ፣ ነገሥታትም ወደ ንጋትሽ ጸዳል ይመጣሉ። “ቀና በዪ፤ ዙሪያሽን ተመልከቺ፤ ሁሉም ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ፣ ሴቶች ልጆችሽም በዕቅፍ ወደ አንቺ ይመጣሉ። ከዚያም ታያለሽ፤ ታብረቀርቂአለሽ፤ ልብሽ ይዘልላል፤ በደስታም ይሞላል። በባሕሮች ያለው ሀብት ወደ አንቺ ይመጣል፤ የነገሥታትም ብልጽግና የአንቺ ይሆናል። የግመል መንጋ፣ የምድያምና የጌፌር ግልገል ግመሎች ምድርሽን ይሞላሉ፤ ወርቅና ዕጣን ይዘው፣ የእግዚአብሔርን ምስጋና እያወጁ፣ ሁሉም ከሳባ ይመጣሉ። የቄዳር የበግ መንጋ ሁሉ ወደ አንቺ ይሰበሰባል፤ የነባዮት አውራ በጎች ያገለግሉሻል። እነዚህም በመሠዊያዬ ላይ ተቀባይነት የሚኖራቸው መሥዋዕቶች ይሆናሉ፤ እኔም የክብር መቅደሴን ግርማ አጐናጽፈዋለሁ። “ርግቦች ወደ ጐጇቸው እንደሚበርሩ፣ እንደ ደመና የሚጓዙ እነዚህ እነማን ናቸው? በርግጥ ደሴቶች እኔን ተስፋ ያደርጋሉ፤ እርሱ ክብሩን ስላጐናጸፈሽ፣ ለእስራኤል ቅዱስ፣ ለእግዚአብሔር አምላክሽ ክብር፣ ከሩቅ ወንዶች ልጆችሽን፣ ከነብራቸውና ከነወርቃቸው ለማምጣት፣ የተርሴስ መርከቦች ቀድመው ይወጣሉ። “ባዕዳን ቅጥሮችሽን ይሠራሉ፤ ነገሥታቶቻቸው ያገለግሉሻል፤ በቍጣዬ ብመታሽም፣ ርኅራኄዬን በፍቅር አሳይሻለሁ። በሮችሽ ምን ጊዜም የተከፈቱ ይሆናሉ፤ ቀንም ሆነ ሌሊት ከቶ አይዘጉም፤ ይህም ሰዎች የመንግሥታትን ብልጽግና ወደ አንቺ እንዲያመጡ፣ ነገሥታታቸውም በድል ወደ አንቺ እንዲገቡ ነው። ለአንቺ የማይገዛ ሕዝብና መንግሥት ይጠፋል፤ ፈጽሞም ይደመሰሳል። “የመቅደሴን ቦታ ለማስጌጥ፣ የሊባኖስ ክብር፣ ጥዱ፣ አስታውና ባርሰነቱ በአንድነት ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ እግሬ የሚያርፍበትንም ስፍራ አከብራለሁ።
ኢሳይያስ 60 ያንብቡ
ያዳምጡ ኢሳይያስ 60
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኢሳይያስ 60:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች