ኢሳይያስ 53:7-12

ኢሳይያስ 53:7-12 NASV

ተጨነቀ፤ ተሠቃየም፤ ነገር ግን አፉን አልከፈተም፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ በሸላቾች ፊት ዝም እንደሚል በግ፣ አፉን አልከፈተም። በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኀጢአት ተመትቶ፣ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ፣ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? በአፉም ሳያታልል፣ ዐመፃም ሳያደርግ፣ አሟሟቱ ከክፉዎች፣ መቃብሩም ከባለጠጎች ጋራ ሆነ። መድቀቁና መሠቃየቱ ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር፤ እግዚአብሔር ነፍሱን የኀጢአት መሥዋዕት ቢያደርገውም እንኳ፣ ዘሩን ያያል፤ ዕድሜውም ይረዝማል፤ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። ከነፍሱ ሥቃይ በኋላ፣ የሕይወት ብርሃን ያያል፤ ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬ በዕውቀቱ ብዙዎቹን ያጸድቃል፤ መተላለፋቸውንም ይሸከማል። ስለዚህ ድርሻውን ከታላላቆች ጋራ እሰጠዋለሁ፤ ምርኮውን ከኀያላን ጋራ ይካፈላል፤ እስከ ሞት ድረስ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠቱ፣ ከክፉ አድራጊዎችም ጋራ በመቈጠሩ፣ የብዙዎችን ኀጢአት ተሸከመ፤ ስለ ዐመፀኞችም ማለደ።