ኢሳይያስ 53:3-10

ኢሳይያስ 53:3-10 NASV

በሰዎች የተናቀና የተጠላ፣ የሕማም ሰውና ሥቃይ ያልተለየው ነበር። ሰዎች ፊታቸውን እንደሚያዞሩበት ዐይነት፣ የተናቀ ነበር፤ እኛም አላከበርነውም። በርግጥ እርሱ ደዌያችንን ወሰደ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ፤ እኛ ግን በእግዚአብሔር እንደ ተመታ፣ እንደ ተቀሠፈ፣ እንደ ተሠቃየም ቈጠርነው። ነገር ግን እርሱ ስለ መተላለፋችን ተወጋ፤ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ በርሱ ላይ የወደቀው ቅጣት ለእኛ ሰላም አመጣልን፤ በርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ እያንዳንዳችንም በየመንገዳችን ነጐድን፤ እግዚአብሔርም፣ የሁላችንን በደል በርሱ ላይ ጫነው። ተጨነቀ፤ ተሠቃየም፤ ነገር ግን አፉን አልከፈተም፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ በሸላቾች ፊት ዝም እንደሚል በግ፣ አፉን አልከፈተም። በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኀጢአት ተመትቶ፣ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ፣ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? በአፉም ሳያታልል፣ ዐመፃም ሳያደርግ፣ አሟሟቱ ከክፉዎች፣ መቃብሩም ከባለጠጎች ጋራ ሆነ። መድቀቁና መሠቃየቱ ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር፤ እግዚአብሔር ነፍሱን የኀጢአት መሥዋዕት ቢያደርገውም እንኳ፣ ዘሩን ያያል፤ ዕድሜውም ይረዝማል፤ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል።