“እናንተ ጽድቅን የምትከታተሉ፣ እግዚአብሔርን የምትፈልጉ ስሙኝ፤ ተቈርጣችሁ የወጣችሁበትን ዐለት፣ ተቈፍራችሁ የወጣችሁባትንም ጕድጓድ ተመልከቱ። ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም፣ ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሣራ ተመልከቱ፤ በጠራሁት ጊዜ አንድ ራሱን ብቻ ነበር፤ ባረክሁት፤ አበዛሁትም። እግዚአብሔር ጽዮንን በርግጥ ያጽናናታል፤ ፍርስራሾቿንም በርኅራኄ ይመለከታል፤ ምድረ በዳዋን እንደ ዔድን፣ በረሓዋንም እንደ እግዚአብሔር ተክል ቦታ ያደርጋል፤ ተድላና ደስታ፣ ምስጋናና የዝማሬ ድምፅ በርሷ ይገኛሉ። “ወገኔ ሆይ፤ አድምጠኝ፤ ሕዝቤ ሆይ፤ ስማኝ፤ ሕግ ከእኔ ይወጣል፤ ፍርዴም ለሕዝቦች ብርሃን ይሆናል። ጽድቄ በፍጥነት እየቀረበ፣ ማዳኔም እየደረሰ ነው፤ ክንዴም ለመንግሥታት ፍትሕን ያመጣል፤ ደሴቶች ወደ እኔ ይመለከታሉ፤ ክንዴንም በተስፋ ይጠብቃሉ። ዐይኖቻችሁን ወደ ሰማያት አንሡ፤ ወደ ታች ወደ ምድርም ተመልከቱ፤ ሰማያት እንደ ጢስ በንነው ይጠፋሉ፤ ምድር እንደ ልብስ ታረጃለች፤ ነዋሪዎቿም እንደ ዐሸን ፈጥነው ይረግፋሉ፤ ማዳኔ ግን ለዘላለም ይኖራል፤ ጽድቄም መጨረሻ የለውም። “እናንተ ጽድቅን የምታውቁ፣ ሕጌንም በልባችሁ ያኖራችሁ ሰዎች ስሙኝ፤ ሰዎች ሲዘብቱባችሁ አትፍሩ፤ ሲሰድቧችሁ አትደንግጡ። ብል እንደ ልብስ ይበላቸዋል፤ ትል እንደ በግ ጠጕር ይውጣቸዋል፤ ጽድቄ ግን ለዘላለም፣ ማዳኔም ከትውልድ እስከ ትውልድ ጸንታ ትኖራለች።” የእግዚአብሔር ክንድ ሆይ፤ ተነሥ፤ ተነሥ! ኀይልን ልበስ፤ እንዳለፉት ዘመናት፣ በጥንት ትውልዶችም እንደ ሆነው ሁሉ ተነሥ። ረዓብን የቈራረጥህ፣ ታላቁን ዘንዶ የወጋህ አንተ አይደለህምን? የዳኑት እንዲሻገሩ ባሕሩን፣ የታላቁን ጥልቅ ውሆች ያደረቅህ፣ በጥልቁም ውስጥ መንገድ ያበጀህ፣ አንተ አይደለህምን? እግዚአብሔር የተቤዣቸው ይመለሳሉ፤ በዝማሬ ወደ ጽዮን ይገባሉ፤ ዘላለማዊ ደስታን ይጐናጸፋሉ፤ ደስታና ሐሤት ይቀድማሉ፤ ሐዘንና ትካዜም ይሸሻሉ። “የማጽናናችሁ እኔ፣ እኔው ብቻ ነኝ፤ ሟች የሆኑትን ሰዎች፣ እንደ ሣር የሚጠወልጉትን የሰው ልጆች ለምን ትፈራለህ? የፈጠረህን፣ ሰማያትን የዘረጋውን፣ ምድርን የመሠረተውን እግዚአብሔርን ረስተሃል፤ ሊያጠፋህ ከተዘጋጀው፣ ከጨቋኙ ቍጣ የተነሣ፣ በየቀኑ በሽብር ትኖራለህ፤ ታዲያ የጨቋኙ ቍጣ የት አለ? ዐንገታቸውን የደፉ እስረኞች በፍጥነት ነጻ ይወጣሉ፤ በታሰሩበትም ጕድጓድ ውስጥ አይሞቱም፤ እንጀራ አያጡም። ሞገዱ እንዲተምም ባሕሩን የማናውጥ፣ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝና፤ ስሙም የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። ቃሌን በአፍህ አኖርሁ፤ በእጄ ጥላ ጋረድሁህ፤ ሰማያትን በስፍራቸው ያስቀመጥሁ፣ ምድርን የመሠረትሁ፣ ጽዮንንም፣ ‘አንቺ ሕዝቤ ነሽ’ ያልሁ እኔ ነኝ።”
ኢሳይያስ 51 ያንብቡ
ያዳምጡ ኢሳይያስ 51
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኢሳይያስ 51:1-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች