እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የግብጽ ሀብትና የኢትዮጵያ ንግድ፣ ቁመተ ረዣዥሞቹ የሳባ ሰዎች፣ ወደ አንተ ይመጣሉ፤ የአንተ ይሆናሉ፤ ከኋላ ይከተሉሃል፤ በሰንሰለትም ታስረው ወደ አንተ በመምጣት፣ በፊትህ እየሰገዱ፣ ‘በእውነት እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ነው፤ ከርሱም በቀር ሌላ አምላክ የለም’ ብለው ይለምኑሃል።” አዳኙ የእስራኤል አምላክ ሆይ፤ አንተ በእውነት ራስህን የምትሰውር አምላክ ነህ። የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ሁሉ ያፍራሉ፤ ይቀልላሉ፤ በአንድነት ይዋረዳሉ። እስራኤል ግን በእግዚአብሔር፣ በዘላለም ድነት ይድናል፤ እናንተም ለዘላለም፣ አታፍሩም፤ አትዋረዱም። ሰማያትን የፈጠረ፣ እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ምድርን ያበጃት፣ የሠራት፣ የመሠረታት፣ የሰው መኖሪያ እንጂ፣ ባዶ እንድትሆን ያልፈጠራት፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም። በጨለማ ምድር፣ በምስጢር አልተናገርሁም፤ ለያዕቆብም ዘር፣ ‘በከንቱ ፈልጉኝ’ አላልሁም። እኔ እግዚአብሔር ጽድቅን እናገራለሁ፤ ትክክለኛውንም ነገር ዐውጃለሁ። “በአንድነት ተሰብሰቡ፤ ቅረቡም፤ እናንተ ከአሕዛብ የኰበለላችሁ፣ ኑ። የዕንጨት ጣዖት የሚሸከሙ፣ ማዳን ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ፣ ዕውቀት የላቸውም። ጕዳያችሁን ተናገሩ፤ አቅርቡ፤ ተሰብስበውም ይማከሩ። ይህን አስቀድሞ ማን ዐወጀ? ከጥንትስ ማን ተናገረ? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? ጻድቅና አዳኝ የሆነ አምላክ፣ ከእኔ በቀር ማንም የለም፤ ከእኔ ሌላ አምላክ የለም። “እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፣ እኔ አምላክ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና፤ ትድኑ ዘንድ ወደ እኔ ተመለሱ። ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፤ ምላስም ሁሉ በእኔ ይምላል፤ ብዬ በራሴ ምያለሁ፤ የማይታጠፍ ቃል፣ ከአፌ በጽድቅ ወጥቷል። ስለ እኔም ሲናገሩ፣ ‘ጽድቅና ኀይል፣ በእግዚአብሔር ብቻ ነው’ ይላሉ።” በርሱ ላይ በቍጣ የተነሡ ሁሉ፣ ወደ እርሱ መጥተው ያፍራሉ። ነገር ግን የእስራኤል ዘር ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ይጸድቃሉ፤ ሞገስንም ያገኛሉ።
ኢሳይያስ 45 ያንብቡ
ያዳምጡ ኢሳይያስ 45
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኢሳይያስ 45:14-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች