ጣዖት የሚሠሩ ሁሉ ከንቱዎች፣ የሚሠሩባቸውም ነገሮች ዋጋ ቢስ ናቸው፤ የሚናገሩላቸው ዕውሮች ናቸው፤ ዕውቀት የላቸውም ያፍራሉም። ለምንም የማይጠቅመውን አምላክ የሚቀርጽ፣ ጣዖትን የሚያበጅስ ማነው? የእጅ ጥበብ ባለሙያው ሰው እንጂ ሌላ አይደለም፤ እርሱና መሰሎቹም ያፍራሉ፤ ሁሉም ተሰብስበው በአንድ ላይ ይቁሙ፤ ይደነግጣሉ፤ ይዋረዳሉም። የብረት የእጅ ጥበብ ባለሙያ መሥሪያን ይይዛል፤ በከሰል ፍም ላይ ይሠራዋል፤ ጣዖትን በመዶሻ ቅርጽ ይሰጠዋል፤ በክንዱም ኀይል ያበጀዋል። ከዚያም ይራባል፤ ጕልበት ያጣል፤ ውሃ ይጠማል፤ ይደክማል። የእጅ ጥበብ ባለሙያ በገመድ ይለካል፤ በጠመኔ ንድፍ ያወጣል፤ በመሮ ይቀርጸዋል፤ በጸርከል ምልክት ያደርግበታል። በሰው አምሳል ይቀርጸዋል፤ የሰውንም ውበት ያለብሰዋል፤ በማምለኪያም ስፍራ ያስቀምጠዋል። ዝግባ ይቈርጣል፤ ሾላ ወይም ወርካ ይመርጣል፤ በደን ውስጥ ካሉት ዛፎች ጋራ እንዲያድግ ይተወዋል፤ ወይም ጥድን ይተክላል፤ ያንም ዝናም ያሳድገዋል። ሰው ለማገዶ ይጠቀምበታል፤ ከዚያም ጥቂት ወስዶ በማንደድ ይሞቀዋል፤ እንጀራም ይጋግርበታል። ከዚሁ ጠርቦ አምላክ ያበጃል፤ ያመልከዋል፤ ጣዖትን ይሠራል፤ ወድቆም ይሰግድለታል። ግማሹን ዕንጨት ያነድደዋል፤ በላዩ ምግቡን ያበስልበታል፤ ሥጋ ጠብሶበት እስኪጠግብ ይበላል፤ እሳቱን እየሞቀ እንዲህ ይላል፤ “ዕሠይ ሞቀኝ፤ እሳቱም ይታየኛል።” በቀረው ዕንጨት የጣዖት አምላኩን ይሠራበታል፤ ወድቆ ይሰግድለታል፤ ያመልከዋል፤ ወደ እርሱም እየጸለየ፣ “አንተ አምላኬ ነህ፤ አድነኝ!” ይላል። ምንም አያውቁም፤ አያስተውሉም፤ እንዳያዩ ዐይናቸው ተሸፍኗል፤ እንዳያስተውሉ ልባቸው ተዘግቷል። ማንም ቆም ብሎ አላሰበም፤ ዕውቀት ወይም ማስተዋል ስለሌለው እንዲህ ማለት አልቻለም፤ “ግማሹን በእሳት አቃጥዬዋለሁ፤ በፍሙ እንጀራ ጋግሬበታለሁ፤ ሥጋ ጠብሼበት በልቻለሁ፤ ታዲያ፣ በቀረው እንዴት ጸያፍ ነገር እሠራለሁ? ለግንድስ መስገድ ይገባኛልን?” ዐመድ ይቅማል፤ ተታላይ ልብ አስቶታል፤ ራሱን ለማዳን አይችልም፤ “ይህ በቀኝ እጄ ያለው ነገር ሐሰት አይደለምን?” ለማለት አልቻለም።
ኢሳይያስ 44 ያንብቡ
ያዳምጡ ኢሳይያስ 44
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኢሳይያስ 44:9-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች