ኢሳይያስ 43:1-28

ኢሳይያስ 43:1-28 NASV

አሁን ግን፣ ያዕቆብ ሆይ የፈጠረህ፣ እስራኤል ሆይ! የሠራህ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህ ጠርቼሃለሁ፤ አንተ የእኔ ነህ፤ በውሃ ውስጥ በምታልፍበት ጊዜ፣ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ ወንዙን ስትሻገረው፣ አያሰጥምህም፤ በእሳት ውስጥ ስትሄድ፣ አያቃጥልህም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም። እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የእስራኤልም ቅዱስ መድኀኒትህ ነኝና፤ ግብጽን ለአንተ ቤዛ እንድትሆን፣ ኢትዮጵያንና ሳባን በአንተ ፈንታ እሰጣለሁ። ለዐይኔ ብርቅና ክቡርም ስለ ሆንህ፣ እኔም ስለምወድድህ፣ ሰዎችን በአንተ ምትክ፣ ሕዝቦችንም በሕይወትህ ፈንታ እሰጣለሁ። ከአንተ ጋራ ነኝና አትፍራ፤ ልጆችህን ከምሥራቅ አመጣለሁ፤ ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ። ሰሜንን፣ ‘አምጣ!’ ደቡብንም፣ ‘ልቀቅ’ እላለሁ፤ ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ፣ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፣ በስሜ የተጠራውን ሁሉ፣ ለክብሬ የፈጠርሁትን፣ ያበጀሁትንና የሠራሁትን አምጡ።” ዐይን እያላቸው የታወሩትን፣ ጆሮ እያላቸው የደነቈሩትን አውጣ። ሕዝብ ሁሉ በአንድነት ይሰብሰብ፤ ሰውም ይከማች፤ ከእነርሱ አስቀድሞ ይህን የነገረን፣ የቀድሞውን ነገር ያወጀልን ማን ነው? ሌሎችን ሰምተው፣ “እውነት ነው” እንዲሉ፣ ትክክለኝነታቸውም እንዲረጋገጥ ምስክሮቻቸውን ያቅርቡ። “ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ፣ እርሱ እኔ እንደ ሆንሁ ትረዱ ዘንድ፣ እናንተ ምስክሮቼ፣ የመረጥሁትም ባሪያዬ ናችሁ” ይላል እግዚአብሔር። “ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም፤ ከእኔም በኋላ አይኖርም። እኔ፣ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም ሌላ የሚያድን የለም። ገልጫለሁ፤ አድኛለሁ፤ ተናግሬአለሁ፤ በመካከላችሁ እኔ እንጂ ባዕድ አምላክ አልነበረም። እኔ አምላክ እንደ ሆንሁ፣ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ከጥንት ጀምሮ እኔው ነኝ፤ ከእጄም ማውጣት የሚችል የለም፤ እኔ የምሠራውን ማን ማገድ ይችላል?” የእግዚአብሔር የእስራኤል ቅዱስ፣ የሚቤዣችሁ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ እናንተ በባቢሎን ላይ ሰራዊት እሰድዳለሁ፤ በሚመኩባቸውም መርከቦች፣ ባቢሎናውያንን ሁሉ እንደ ኰብላይ አመጣለሁ። እኔ እግዚአብሔር፣ የእናንተ ቅዱስ፣ የእስራኤል ፈጣሪ፣ ንጉሣችሁ ነኝ።” በባሕር ውስጥ መንገድ፣ በማዕበል ውስጥ መተላለፊያ ያበጀ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እንደ ገና ላይነሡ እዚያው እንዲተኙ፣ እንደ ጧፍ ኵስታሪ ረግፈው እንዲጠፉ፣ ሠረገሎችንና ፈረሶችን፣ ሰራዊቱንና ደጀኑን በአንድነት ያወጣ እንዲህ ይላል፤ “የቀደመውን ነገር አታስቡ፤ ያለፈውን እርሱ። እነሆ፤ አዲስ ነገር አደርጋለሁ! እርሱም አሁን ይበቅላል፤ አታስተውሉትምን? በምድረ በዳም መንገድ አዘጋጃለሁ፤ በበረሓም ምንጭ አፈልቃለሁ፤ የምድረ በዳ አራዊት፣ ቀበሮና ጕጕት ያከብሩኛል፤ በምድረ በዳ ውሃ፣ በበረሓም ምንጭ እሰጣለሁና። ለመረጥሁት ሕዝቤ ውሃ እሰጣለሁ፤ ለራሴ ያበጀሁት ሕዝብ ምስጋናዬን ያውጅ ዘንድ ይህን አደርጋለሁ። “ያዕቆብ ሆይ፤ አንተ ግን አልጠራኸኝም፤ እስራኤል ሆይ፤ የእኔ ነገር ታክቶሃል። ለሚቃጠል መሥዋዕት በጎች አላመጣህልኝም፤ በመሥዋዕትህም አላከበርኸኝም። በእህል ቍርባን እንድታገለግለኝ አላስቸገርሁህም፤ በዕጣን መሥዋዕትም አላሰለቸሁህም። መልካም መዐዛ ያለው ከሙን አልገዛህልኝም፤ በመሥዋዕትህ ሥብ አላጠገብኸኝም፤ ነገር ግን በኀጢአትህ አስቸገርኸኝ፤ በበደልህም አደከምኸኝ። “ስለ ራሴ ስል መተላለፍህን የምደመስስልህ፣ እኔ፣ እኔው ነኝ፤ ኀጢአትህን አላስባትም። እስኪ ያለፈውን አስታውሰኝ፤ ተቀራርበን እንከራከርበት፤ ትክክለኛ ስለ መሆንህም አስረዳ። የመጀመሪያው አባትህ ኀጢአት ሠርቷል፤ መምህሮችህም ዐምፀውብኛል። ስለዚህ የመቅደስህን አለቆች አዋርዳለሁ፤ ያዕቆብን ለጥፋት፣ እስራኤልን ለስድብ እዳርጋለሁ።