ኢሳይያስ 42:18-25

ኢሳይያስ 42:18-25 NASV

“እናንተ ደንቈሮዎች ስሙ፤ እናንተ ዕውሮች እዩ፤ ተመልከቱም! አገልጋዬ እንጂ፣ ሌላ ዕውር ማን አለ? ከምልከው መልእክተኛዬስ በቀር ማን ደንቈሮ አለ? ለእኔ ታማኝ እንደ ሆነ ሰው የታወረ፣ እንደ እግዚአብሔርስ አገልጋይ ዕውር ማነው? ብዙ ነገርን አያችሁ፤ ነገር ግን አላስተዋላችሁም፤ ጆሯችሁ ክፍት ነው፤ ነገር ግን ምንም አትሰሙም።” እግዚአብሔር ስለ ጽድቁ ሲል፣ ሕጉን ታላቅና የተከበረ በማድረግ ደስ አለው። ይህ ሕዝብ ግን የተበዘበዘና የተዘረፈ፣ በጕድጓድ ውስጥ የተጠመደበት፣ በወህኒ ቤት የተዘጋበት ነው፤ ተበዝብዘዋል፣ የሚያድናቸውም የለም፤ ተማርከዋል፣ “መልሷቸው” የሚልም የለም። ከእናንተ ይህን የሚሰማ፣ ለሚመጣውም ጊዜ አስተውሎ የሚያደምጥ ማነው? ያዕቆብን ለዝርፊያ፣ እስራኤልን ለምርኮ የዳረገ ማነው? በኀጢአት የበደልነው፣ እግዚአብሔር አይደለምን? መንገዱን ለመከተል፣ ለሕጉም መታዘዝ አልፈለጉምና። ስለዚህ የሚነድድ ቍጣውን፣ የጦርነትንም መዓት አፈሰሰባቸው፤ በእሳት ነበልባል ከበባቸው፤ እነርሱ ግን አላስተዋሉም፤ አቃጠላቸው፤ እነርሱ ግን ልብ አላሉም።