ኢሳይያስ 24:1-23

ኢሳይያስ 24:1-23 NASV

እነሆ፤ እግዚአብሔር ምድርን ባድማ ያደርጋታል፤ ፈጽሞ ያጠፋታል፤ የፍርስራሽ ክምር ያደርጋታል፤ ነዋሪዎቿንም ይበትናል። ነገሩ ሁሉ አንድ ዐይነት ይሆናል፤ በሕዝቡ ላይ የሚሆነው በካህኑ፣ በአገልጋዩ ላይ የሚሆነው በጌታው፣ በአገልጋይዋ ላይ የሚሆነው በእመቤቷ፣ በገዥው ላይ የሚሆነው በሻጩ፣ በተበዳሪው ላይ የሚሆነው በአበዳሪው፣ በብድር ከፋይ ላይ የሚሆነው በብድር ሰጪው ይሆናል። ምድር ፈጽሞ ባድማ ትሆናለች፤ ጨርሶም ትበዘበዛለች፤ እግዚአብሔር ይህን ቃል ተናግሯልና። ምድር ትደርቃለች፤ ትረግፋለች፤ ዓለም ትዝላለች፤ ትረግፋለች፤ የምድርም መሳፍንት ይዝላሉ። ምድር በሕዝቧ ትረክሳለች፤ ሕግን ጥሰዋል፤ ሥርዐትን ተላልፈዋል፤ ዘላለማዊውንም ኪዳን አፍርሰዋል። ስለዚህ ርግማን ምድርን ትበላለች፤ ሕዝቦቿም ስለ በደላቸው ይቀጣሉ፤ ስለዚህ የምድር ነዋሪዎች ተቃጥለዋል፤ በጣም ጥቂት የሆኑት ቀርተዋል። አዲሱ የወይን ጠጅ ዐለቀ፤ የወይኑም ተክል ደረቀ፤ ደስተኞችም ሁሉ አቃሰቱ። የከበሮ ደስታ ጸጥ አለ፤ የጨፋሪዎች ጩኸት አበቃ፤ ደስ የሚያሠኘውም በገና እረጭ አለ። ከእንግዲህ እየዘፈኑ የወይን ጠጅ አይጠጡም፤ መጠጡም ለሚጠጡት ይመርራል። የፈራረሰችው ከተማ ባድማ ሆነች፤ የየቤቱም መግቢያ ተዘጋ። በየአደባባዩ የወይን ጠጅ ያለህ እያሉ ይጮኻሉ፤ ደስታው ሁሉ ወደ ሐዘን ይለወጣል፤ ሐሤቱም ሁሉ ከምድር ገጽ ጠፍቷል። ከተማዪቱ ፈጽማ ፈርሳለች፤ በሮቿም ደቅቀው ወድቀዋል። የወይራ ዛፍ ሲመታ፣ የወይንም ዘለላ ሲቈረጥ ቃርሚያ እንደሚቀር ሁሉ፣ በምድሪቱ ላይ፣ በሕዝቦችም ላይ እንዲሁ ይሆናል። ድምፃቸውን ከፍ ያደርጋሉ፤ በደስታም ይጮኻሉ፤ ከምዕራብም የእግዚአብሔርን ክብር ያስተጋባሉ። ስለዚህ በምሥራቅ ለእግዚአብሔር ክብር ስጡ፤ ከባሕር ደሴቶችም፣ የእስራኤልን አምላክ፣ የእግዚአብሔርን ስም ከፍ ከፍ አድርጉ። “ለጻድቁ ክብር ይሁን” የሚል ዝማሬ፣ ከምድር ዳርቻ ሰማን። እኔ ግን፣ “ከሳሁ፤ መነመንሁ፤ ወዮልኝ! ከዳተኞች አሳልፈው ሰጡ፤ ከዳተኞች በክሕደታቸው አሳልፈው ሰጡ” አልሁ። በምድር የምትኖር ሕዝብ ሆይ፤ ሽብር፣ ጕድጓድና ወጥመድ ይጠብቁሃል። ከሽብር ድምፅ የሚሸሽ፣ ወደ ጕድጓድ ይገባል፤ ከጕድጓድ የወጣም፣ በወጥመድ ይያዛል። የሰማይ መስኮቶች ተከፍተዋልና፤ የምድርም መሠረት ተናወጠ። ምድር ተከፈለች፤ ምድር ተሰነጠቀች፤ ምድር ፈጽማ ተናወጠች። ምድር እንደ ሰካራም ዞረባት፤ ነፋስ እንደሚወዘውዘውም ጐጆ ሆነች፣ የዐመፅዋ ሸክም ከባድ ስለ ሆነ ትወድቃለች፤ እንደ ገናም አትነሣም። በዚያ ቀን እግዚአብሔር፣ በላይ በሰማያት ያሉትን ኀይሎች፣ በታችም በምድር ያሉትን ነገሥታት ይቀጣቸዋል። በጕድጓድ ውስጥ እንዳሉ እስረኞች፣ በአንድ ላይ ይታጐራሉ፤ በእስር ቤት ይዘጋባቸዋል፣ ከብዙ ቀንም በኋላ ለፍርድ ይቀርባሉ። የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም፣ በሽማግሌዎቹም ፊት በክብሩ ይነግሣል፤ ጨረቃ ትሸማቀቃለች፤ ፀሓይም ታፍራለች።