ኢሳይያስ 2
2
የእግዚአብሔር ተራራ
1የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ይህ ነው፤
2በዘመኑም ፍጻሜ፣
የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ
ከተራሮች ከፍ ብሎ ይመሠረታል፤
ከኰረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤
ሕዝቦችም ሁሉ ወደዚያ ይጐርፋሉ።
3ብዙ አሕዛብ መጥተው እንዲህ ይላሉ፤
“ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣
ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤
በጐዳናውም እንድንሄድ፤
መንገዱን ያስተምረናል።”
ሕግ ከጽዮን፣
የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና።
4እርሱ በሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤
የብዙ ሰዎችን አለመግባባት ያስወግዳል።
እነርሱም ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ፣
ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጋሉ።
ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፤
ጦርነትንም ከእንግዲህ አይማሩም።
5እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፤ ኑ፤
በእግዚአብሔር ብርሃን እንመላለስ።
የእግዚአብሔር ቀን
6የያዕቆብ ቤት የሆነውን
ሕዝብህን ትተሃል፤
እነርሱ በምሥራቅ ሰዎች ከንቱ አምልኮ ተሞልተዋልና፤
እንደ ፍልስጥኤማውያን ያሟርታሉ፤
ከባዕዳን ጋራ አገና ይማታሉ።
7ምድራቸው በብርና በወርቅ ተሞልታለች፤
ሀብታቸውም ልክ የለውም።
ምድራቸው በፈረሶች ተሞልታለች፤
የሠረገሎቻቸውም ብዛት ልክ የለውም።
8ምድራቸው በጣዖታት ተሞልታለች፤
ጣቶቻቸው ላበጇቸው፣
ለእጆቻቸው ሥራ ይሰግዳሉ።
9ሰው ዝቅ ብሏል፤
የሰው ልጅም ተዋርዷል፤
ስለዚህ በደላቸውን ይቅር አትበል#2፥9 ወይም፣ ከፍ አታድርጋቸው ማለት ነው።።
10ከእግዚአብሔር አስፈሪነትና ከግርማው ሽሽ፤
ወደ ዐለቶች ሂድ፤
በመሬትም ውስጥ ተሸሸግ።
11የእብሪተኛ ሰው ዐይን ይሰበራል፤
የሰዎችም ትዕቢት ይዋረዳል፤
በዚያ ቀን እግዚአብሔር ብቻውን ከፍ ከፍ ይላል።
12የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር
እብሪተኛውንና ትዕቢተኛውን ሁሉ፣
የተኵራራውን በሙሉ
የሚያዋርድበት ቀን አለው።
13ረዥምና ከፍ ከፍ ያሉትን የሊባኖስ ዝግባዎች ሁሉ፣
የባሳንን የወርካ ዛፎች ሁሉ፣
14ታላላቁን ተራራ ሁሉ፣
ከፍ ያለውን ኰረብታ ሁሉ፣
15ረዣዥሙን ግንብ ሁሉ፣
የተመሸገውን ቅጥር ሁሉ፣
16የተርሴስን መርከቦች#2፥16 በዕራይስጡ ለሁሉ የተርሴስ መርከቦች ይላል። ሁሉ፣
የክብር ጀልባዎችን ሁሉ የሚያዋርድበት ቀን አለው።
17የሰው እብሪት ይዋረዳል፤
የሰውም ኵራት ይወድቃል፤
በዚያ ቀን እግዚአብሔር ብቻ ከፍ ከፍ ይላል፤
18ጣዖቶች ሁሉ ፈጽሞ ይወድማሉ።
19 እግዚአብሔር ምድርን ለማናወጥ በሚነሣበት ጊዜ፣
ሰዎች ከአስፈሪነቱ
ከግርማውም የተነሣ፣
ወደ ዐለት ዋሻ፣
ወደ መሬትም ጕድጓድ ለመሸሸግ ይሮጣሉ።
20በዚያ ቀን ሰዎች
ሊያመልኳቸው ያበጇቸውን፣
የብርና የወርቅ ጣዖቶቻቸውን
ለፍልፈልና ለሌሊት ወፍ ይወረውራሉ።
21 እግዚአብሔር ምድርን ለማናወጥ በሚነሣበት ጊዜ፣
ሰዎች ከአስፈሪነቱ
እንዲሁም ከግርማው የተነሣ፣
ወደ ድንጋይ ዋሻ፣
ወደ ዐለት ስንጣቂ ሮጠው ይገባሉ።
22እስትንፋስ አፍንጫው ላይ ባለች
በሰው አትታመኑ፤
ከቶ ምን የሚበጅ ነገር አለው!
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.