ኢሳይያስ 11:10-16

ኢሳይያስ 11:10-16 NASV

በዚያም ቀን፣ የእሴይ ሥር ለሕዝቦች ምልክት ሆኖ ይቆማል፤ አሕዛብ እርሱን ይፈልጋሉ፤ ማረፊያውም የከበረ ይሆናል። በዚያ ቀን፣ ጌታ እጁን ዘርግቶ እንደ ገና የተረፈውን የሕዝቡን ቅሬታ ከአሦር፣ ከግብጽ፣ ከጳትሮስ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከኤላም፣ ከባቢሎን፣ ከሐማትና ከባሕር ጠረፍ ምድር ይሰበስባል። ለመንግሥታት ምልክትን ያቆማል፤ ከእስራኤልም የተሰደዱትን መልሶ ያመጣቸዋል፤ የተበተኑትን የይሁዳ ሕዝብ፣ ከአራቱ የምድር ማእዘን ይሰበስባል። የኤፍሬም ምቀኛነት ያከትማል፤ የይሁዳ ጠላቶችም ይቈረጣሉ፤ ኤፍሬም በይሁዳ አይቀናም፤ ይሁዳም ኤፍሬምን አይጠላም። በምዕራብ በኩል በፍልስጥኤም ተረተር ላይ ይወርዳሉ፤ ሁለቱም ተባብረው በምሥራቅ ያለውን ሕዝብ ይዘርፋሉ፤ በኤዶምና በሞዓብ ላይ እጃቸውን ያነሣሉ፤ አሞናውያንም ይገዙላቸዋል። እግዚአብሔር በሚጋረፍም ነፋስ፣ የግብጽን ባሕረ ሰላጤ ያደርቃል፤ እጁን በኤፍራጥስ ወንዝ ላይ ይዘረጋል፤ ሰባት ታናናሽ ጅረትም አድርጎ ይለያየዋል፤ ስለዚህ ሰዎች ከነጫማቸው መሻገር ይችላሉ። እስራኤል ከግብጽ በወጣ ጊዜ እንደ ሆነው ሁሉ፣ ከአሦር ለተረፈው ቅሬታ ሕዝብ፣ እንዲሁ ጐዳና ይዘጋጅለታል።